ለ190 የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱን ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ዘርፋን ለማነቃቃት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው 7 ሚሊዮን 118 ሺህ 784 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ውስጥ በ10 ወሩ 83 በመቶው የሚኾኑት መጎብኘታቸውን ቢሮ ኀላፊው መልካሙ ፀጋዬ ገልጸዋል።

ከዚህም 2 ቢሊዮን 66 ሚሊዮን 515 ሺህ 933 ብር ገቢ ተገኝቷል። ይኽም ከዕቅዱ 57 በመቶ ገደማ ማሳካት ተችሏል። በ10 ወሩ ከጎበኙት ውስጥ 17 ሺህ 99 የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ሲኾኑ 66 ሚሊዮን 137 ሺህ 61 ብር ገቢ ተገኝቷል። ቢሮው የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም እያከናወነ እንደሚገኝ ኀላፊው ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ለቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ የሚውል ግብዓት ለማምረት የኖራ ድንጋይ የሚገኝበትን ቦታ የመለየት ሥራ ተሠርቷል፤ ጨረታም መውጣቱን አንስተዋል።

ኀላፊው እንዳሉት በበጀት ዓመቱ 292 የሆቴል እና የቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታቸውን አጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ኾኗል። ለ190 የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ተችሏል። በዘርፉ ባለፉት 10 ወራት ለ23 ሺህ 369 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ነው የገለጹት። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 7 ሺህ 115 የሚኾኑት በቋሚነት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው።

ባለፉት ወራት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የቱሪዝም ምጣኔ ሃብቱን ማዳከሙን ነው ኀላፊው የገለጹት። በተለይም ደግሞ ኑሯቸውን በዘርፉ ላይ መሠረት ያደረጉ ሠራተኞች፣ አስጎብኝ ማኅበራት እና በዘርፋ የተደራጁ ማኅበራት ችግር ላይ መውደቃቸውን ጠቅሰዋል። የተጠሪ ተቋማት የማቋቋሚያ ደንብ ባለመጽደቁ የመልካም አሥተዳደር ችግር መፍጠሩንም ነው ያነሱት።

በቀጣይ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ ከማድረግ ባለፈ የቋሚ ቅርሶች የይዞታ ማረጋገጫ እና ወሰን ክለላ ደንብ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ፣ የደሴ ሙዚየም ጥገና እና መልሶ የማደራጀት ሥራ፣ የክልሉን ቋንቋዎች መገለጫ መረጃዎች ማዘጋጀት፣ የቱሪስት መሪ መጽሐፍት በማሳተም ማሰራጨት፣ የክልሉን የመስህብ ሃብቶች እና መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ተንቀሳቃሽ ምስል ማዘጋጀት፣ የሪጅኦፓሊታን እና የሜትሮፖሊታንት ከተሞችን የሰው ኃይል ስምሪት ማስተካከል፣ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት የጉዳት መጠኑ የመለየት እና መረጃ የማደራጀት ሥራዎች ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ዋናዎቹ መኾናቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአዕምሮ ጤና ችግር ከብዝኃ-ሕይወት ጋር ግንኙነት አለው” አዲስ የጥናት ውጤት
Next article“ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ዓለም ቢለወጥም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን ባሉበት ናቸው” አንቶኒዮ ጉተሬዝ