“የአዕምሮ ጤና ችግር ከብዝኃ-ሕይወት ጋር ግንኙነት አለው” አዲስ የጥናት ውጤት

42

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለምለም በኾኑ እና ከፍተኛ ብዝኃ-ሕይወት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የተሻለ የአዕምሮ ጤና አላቸው። ምክንያቱ ደግሞ ተፈጥሮ የበዛበት አካባቢ ስሜት የማነቃቃት እና ጭንቀትን የመቀነስ አቅም ስላለው መኾኑን ዊፎረም አዲስ ጥናትን ጠቅሶ ገልጿል::

ብዝኃ-ሕይወት ካለው ጠቀሜታ በመነሳት የከተማ መሠረተ ልማት ሲታሰብ የተፈጥሮ ብዝኃነት ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል ። የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም መረጃ እንደሚያትተው ይህን መሰል ዘገባ አንብበን በምንጨርስበት ወቅት ዓለማችን ቢያንስ አንድ የብዝኃ-ሕይወት ዝርያ እስከ መጨረሻው ታጣለች ይላል።

የሰው ልጅ ጤናማነት በተፈጥሮ ላይ የተመሰረተ በመኾኑ የብዝኃ-ሕይወት መመናመን በሰው ልጅ ሕልውና ላይ ስጋት እንደደቀነ ተጠቁሟል። ከዚህ በፊት የተሠሩ ጥናቶችም ተፈጥሮ እና የአዕምሮ ጤና ያላቸውን ቁርኝት ያረጋግጣሉ። ጽሑፉ ለአብነት ብዝኃ-ሕይወት በብዛት ያለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በዓለማችን በስፋት በሚከሰቱ የድባቴ እና ጭንቀት በሽታዎች የመያዝ እድላቸው በ71 በመቶ ያነሰ ነው።

አዲሱ ጥናት የብዝኃ-ሕይወት መብዛት እና ማነስ በአዕምሮ ጤና ላይ ያለውን የጥቅም ደረጃ እንደሚወስነውም ተገልጿል:: ዛፎች፣ ቁጥቋጦዎች፣ ውኃማ አካላት እና የዱር እንስሳት ያሉበት በብዝኃ-ሕይወት የበለፀገ ስፍራ አናሳ የተፈጥሮ ብዝኃነት ካለባቸው አካባቢዎች የተሻለ የአዕምሮ ጤና በረከትን ይሰጣሉ።

ዊፎረም አዲስ ብሎ ያወጣው ይህ ጥናት እ. ኤ .አ ከሚያዚያ 2018 እስከ መስከረም 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ 1ሺህ 998 ሰዎች በገጠር እና በከተማ አካባቢዎች ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልምድ እንዲያጋሩ አካትቷል። የጥናቱ ውጤት የሚያረጋግጠውም ብዙ የብዝኃ-ሕይወት ያላቸው አካባቢዎች የተሻለ የአዕምሮ ደኅንነት እንዲሰማ የሚያደርጉ መኾኑን ነው።

በብዝኃ-ሕይወት የበለፀጉ አካባቢዎች የተሻለ ትኩረት እንዲኖረን፣ አዕምሮ ረፍት እንዲያገኝ እና ረጅም ትውስታ እንዲኖረን በማድረግ የአዕምሯችንን ጤንነት ይጠብቃሉ። ተፈጥሮ በነገሠባቸው ሥፍራዎች የሚኖሩ ሰዎች በአብዛኛው እንቅስቃሴ በማድረግ እና ከሌሎች ጋር ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር እንደሚያሳልፉም ጥናቱ ጠቁሟል። እንደዚህ ዓይነት የዕለት ውሎዎች ደግሞ ኢንዶርፊን የተባለውን እና ሌሎችን የተሻለ የምቾት ስሜት ለውጥ እንዲኖረን የሚረዱ ሆርሞኖች እንዲመነጩ ያደርጋሉ። ከአዕምሮ ጤና ባለፈ የተፈጥሮ ብዝኃነት ያለበት አካባቢ በካዮችን በመቀነስ እና የከባቢ ሙቀትን በማስተካከል እንደ አለርጂ እና አስም የመሳሰሉ የጤና ችግሮችንም ያስወግዳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽሜጠ ዊከ ጋዜጠ ግንቭት 15/09/2016
Next articleለ190 የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱን ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።