“የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ለቀጣናዊ ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል” አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ

18

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ለቀጣናዊ ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገልጸዋል። አምባሳደር ታዬ ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ሳዑድ አረቢያ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት መሠረት በማድረግ በሰላም፣ በደኅንነት፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ወቅቱ መኾኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሰፍን እንዲሁም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር እያደረገች ላለው ተግባር ሳዑዲ አረቢያ ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

አያይዘውም በሳዑዲ አረቢያ በሥራ ላይ ተሰማርተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ በመኾኑ ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ እንደኾነም አንስተውላቸዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አጋዥ በመኾናቸው የሳዑዲ አረቢያን መንግሥት እገዛ ጠይቀዋል። የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እያደረገች ያለው ሥራ በሀገራቸው በኩል የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የግንኙነት ደረጃው ከዚህ በተሻለ እንዲጠናከር የሳዑዲ አረቢያ ፍላጎት መኾኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እያደረገች ያለውን አዎንታዊ ሰላም እና ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ ተግባር አጠናክራ እንድትቀጥል እና በጋራ ለመሥራትም ዝግጁ መኾናቸውን አሳውቀዋል። የሳዑዲ አረቢያ የቢዝነስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መኾኑ እና ለስኬታማነቱም መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቷ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየሠራች እንደኾነ አብራርተው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን ለማሰማራት በሳዑዲ አረቢያ በኩል እቅድ መኖሩን ማሳወቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የውስጥ ሰላማችንን መጠበቅ ምንጊዜም ለሕዝባችን የልማት ተጠቃሚነት የማይተካ ሚና አለዉ” የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን
Next articleኽሜጠ ዊከ ጋዜጠ ግንቭት 15/09/2016