
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ያሉበትን የሥራ አፈጻጸም ለመገምገም ያለመ ጉብኝት ተካሂዷል። የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ደረጃ የጎበኙት የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እንደገለጹት የሕግ የማስከበርና የልማት ሥራዎችን አቀናጅተን መሥራት መቻላችን አሁን ፕሮጀክቶች ለደረሱበት አመርቂ ውጤት አብቅቶናል ብለዋል።
በዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር የክልሉ መንግሥት በመደበዉ 185 ሚሊዮን ብር ወጭ ከ22 ሺህ ሕዝብ በላይ የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ የሚያደርገዉ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 98 በመቶ መድረሱን ተመልክተናል ብለዋል። 1 ነጥብ5 ሚሊየን ብር ተመድቦለት በግንባታ ላይ ያለዉን የከተማ አሥተዳደሩ የውኃ ጽሕፈት ቤት ቢሮ ግንባታ አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱም ተመላክቷል።
ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት በግንባታ ላይ ያለን የልምጭ ወንዝ መለስተኛ የድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱን ያረጋገጥን ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የሚገነባውን 10 ባለ 2 ክፍል የአቅመ ደካማ የቀበሌ ቤት ሥራ አፈፃፀም 74 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በዋን ዋሽ ፕሮግራም ድጋፍ በ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገነባዉ የመናሀሪያ መፀዳጃ ክፍል ግንባታ ግንባታዉ ተጠናቆ በቅርብ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንደደረሰም ተገልጿል። ዋና አሥተዳዳሪዉ ዱርቤቴ ከተማን በሌሊት ውብና ማራኪ ለማድረግ በከተማዉ ማኅበረሰብ ተሳትፎ የተሠሩ የመስመር ላይ የዲም ላይት መብራቶች ተመልክተናል ያሉ ሲሆን ዱርቤቴ ከተማን ዉብና ማራኪ ለማድረግ በየደረጃዉ ያሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች በጊዜ የለኝም ስሜት ሊሠሩ ይገባል ነዉ ያሉት።
ለልማቱ መፋጠን ማኅበረሰቡ የነበረዉ ተሳትፎ የተሻለ ሲሆን በቀጣይ ሥራዎችም ከአመራሩ ጎን በመሠለፍ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተጠቁሟል። የውስጥ ሰላማችን ምንጊዜም ለሕዝባችን የልማት ተጠቃሚነት የማይተካ ሚና ያለዉ በመኾኑ የአካባቢው ሕዝብ የዉስጥ ሰላሙን በመጠበቅ ለፕሮጀክቶች መጠናቀቅ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ዋና አሥተዳዳሪዉ መልክታቸዉን አስተላልፈዋል። በጉብኝቱ የሰሜን ጎጃም ዞን፣ የወረዳ መሪዎች እና የሰሜን ጎጃም ኮማንድ ፖስት አመራሮች ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!