ከ10 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ የሥነ ምድር ካርታ፣ የማዕድን ፍለጋ እና ክምችት ግመታ ሥራ ለማካሄድ የውል ስምምነት ተደረገ።

38

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ በክልሉ ከሚገኙ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሥነ ምድር ካርታ፣ የማዕድን ፍለጋ እና ክምችት ግመታ ሥራ ለማካሄድ የፊርማ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የክልሉን የማዕድን ሃብት አቅም በማወቅ ወደ ልማት ለማስገባት የሚያስችል እቅድ ነው።

የአማራ ክልል ሰፊ የማዕድን ሃብት እንዳለው የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ታምራት ደምሴ ገልጸዋል። በአማራ ክልል እስከ አሁን በተደረጉ ጥናቶች ከ31 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የማዕድን ፍለጋ፣ ክምችት ግመታ እና የካርታ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ምክትል ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።

ዛሬ ደግሞ ከጎንደር፣ ከባሕር ዳር እና ከወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ከ10 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ የሥነ ምድር ካርታ እና የማዕድን ፍለጋ እና ክምችት ግመታ ሥራ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይኽም የክልሉን የማዕድን ፍለጋ እና ክምችት ግመታ ሥራ ወደ 40 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ያሳድገዋል። እቅዱ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችል ነው።

ቢሮው ከዚህ በፊት በክልሉ ከሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውል መፈራረሙን ምክትል ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። በ2015 ዓ.ም 10 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ከጎንደር፣ ከባሕር ዳር፣ ከወልድያ፣ ከደብረ ብርሃን እና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር ሥምምነት ማድረጉን ገልጸዋል። እስከ አሁን በተደረጉ ጥናቶች ከ40 በላይ ማዕድናት በክልሉ ተገኝተዋል ብለዋል። የተገኙ ማዕድናትን በቀጣይ በባለሃብቶች፣ በምርምር ተቋማት እና በባለሙያዎች ዝርዝር ጥናት ተደርጎባቸው ወደ ሥራ የሚገባ ይኾናል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች እና በዘርፉ የተሠማሩ ተቋማት ከቢሮው ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ሳይንስ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አሸብር ሰውአለ (ዶ.ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ሰባት ፕሮጀክቶችን በመሥራት ለቢሮው አስረክቧል። አሁን ላይም 6 ሺህ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ መሠረታዊ የካርታ ሥራ ለመሥራት ውል መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ቦታውን አጥንቶ ለማስረከብ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አሥተዳደር እና ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ማርየ በለጠ (ዶ.ር) ከዚህ በፊት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የብረት ማዕድን ልየታ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም አጠቃላይ ዝርዝር ጥናት ለማካሄድ ሥምምነት ተደርጓል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዝቋላ ወረዳ የማዕድን ሃብት ልየት ሥራ እንደሚደረግም ነው የገለጹት። የልየታ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ዝርዝር ጥናት የሚደረግ ይኾናል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Caamsaa 15/2016
Next articleበሰሜን ሸዋ ዞን 30 ሺህ 140 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑ ተገለጸ።