
ከሚሴ፡ ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ በደዋ ጨፋ ወረዳ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ወጣቶች “ሌሎችም ነፍጥ ያነሱ አካላት በሙሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ” ጥሪ አቅርበዋል። ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ ወጣቶች የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ለአካባቢያቸው ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
ሌሎች ነፍጥ ያነሱ አካላት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ሕዝብን በልማት መካስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ነፍጥ ያነሱ አካላት ወደሰላም መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ሼህ መሐመድ የሱፍ እና ወይዘሮ ከድጃ አሕመድ በአካባቢያቸው የጸጥታ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ገልጸው እነዚህ ነፍጥ ያነሱ አካላት ወደ ሰላም መምጣታቸው ችግሩን እንደሚፈታ እና በሰላም ለመኖር እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። ሁሉም ነፍጥ ያነሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡም ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
የደዋ ጨፋ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሕመድ አሊ የወረዳውን ሰላም ለማስጠበቅ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥት ነፍጥ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሰረት ወጣቶች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበር የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከዚህ በፊት በተደረገው የሰላም ጥሪ በርካታ ነፍጥ ያነገቡ አካላት ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ኑሮ እየኖሩ መኾኑንም ተጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!