
አዲስ አበባ: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ግልጽ እና ተገማች የኾነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አሥተዳደር፣ እንዲሁም የአከራይና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በኾነ መልኩ የሚያስተናግድ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል። የመኖሪያ ቤት ኪራይን ሥርዓት ሊያስይዝ የሚችል የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አሥተዳደር አዋጅ ላይ የሥልጠና እና ውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሔለን ደበበ መሠረታዊ የሰዎች ፍላጎት የኾነውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመድረኩ ጠቁመዋል። ይህንን ለማሟላት የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አቅርቦትና ፍላጎት ባለመጣጣሙ አሁንም ፈተናዎች ከፊታችን ይጠብቁናል ብለዋል። የግል ዘርፉን ተሳታፊ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት መጣር አስፈላጊ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ከቤት ልማቱ በተጨማሪ የቤት አሥተዳደር ሥራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ አከራይና ተከራይ ሚዛናዊ በኾነ መልኩ ጥቅማቸውና መብታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ጥናቶችን እና የሀገራት ተሞክሮዎችን ወስዶ አዋጅ 1320/2016 እንዲጸድቅ አድርጓል ብለዋል።
በአዋጁ ላይ የጋራ አረዳድ በመፍጠርና የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በፍጥነት ወደ ትግበራ ለመግባት እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል። በሀገራችን ትላልቅ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ እና በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መኾኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
የማኅበረሰቡን አቅም ያገናዘበ እና ተመጣጣኝ እንዲኾን በከተማው ያለውን የመኖሪያ ቤት የኪራይ ንረት መቆጣጠርና ማሥተዳደር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ግልጸኝነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ የአከራይና ተከራይ ጥቅምና መሠረታዊ መብቶች ሚዛን በጠበቀ መልኩ ይገባል ተብሏል። የጸደቀውን የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊነት ተገንዝቦም አዋጁን ተከትለው የሚወጡ የሕግ ማዕቀፎችን ወደ ተግባር በማሸጋገር በቁጥጥርና አሥተዳደር ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋልም ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!