
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ዕቅዶች አፈጻጸምን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በምግብ እና ስርዓተ ምግብ፣ በሰቆጣ ቃል ኪዳን እና በጤና መድህን ላይ የተያዙ ዕቅዶች እና አፈፃፀማቸውን በተመለከተ ዛሬ ከሚመለከታቸው የስራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሉት እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች የማኅበረሰቡን ጠቀሜታ ከፍ ያደረጉ እና ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮዋን ማጋራት የጀመረችባቸው መኾናቸውን አይተናል ብለዋል። ተግባራቱ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፣ የአጋዥ አካላት እንዲሁም የሕዝቡን ትብብር፣ ድጋፍ፣ ትጋት እና ቁርጠኛ ተሳትፎን የሚጠይቁ በመኾናቸው ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ በውይይታችን ተግባብተናል ብለዋል።
የሌማት ትሩፋት እና ፅዱ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ሀገራዊ ፕሮግራሞች ከተግባራቱ ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳላቸው በመጠቆም፤ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅም በውይይቱ መታየቱን ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!