በደብረ ብርሃን ዞናል መናኸሪያ ዲጂታል የትኬት ሽያጭ ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡

23

ደብረ ብርሃን : ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተሳፋሪዎች ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረት ከዛሬ ጀምሮ በደብረ ብርሃን ዞናል መናኸሪያ ዘመናዊ ወይንም ዲጂታል የትኬት ሽያጭ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በትራንስፖርት ዘርፉ በአሽከርካሪዎች እና በተሽከርካሪ ባለንብረቶች አማካኝነት በማናለብኝነት የሚደረግ የታሪፍ ጭማሬ በተጓዦች ላይ ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ አሚኮ ይህ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የዞኑ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት በቅርቡ የትኬት መቁረጫ መስኮት በማዘጋጀት የሕዝቡን ችግር ለመቅረፍ ጥረት አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ መስኮት የሚሰጠው አገልግሎት ሕዝቡን ከታሪፍ ጭማሬ እና እንግልት መታደግ ሳይችል ቆይቷል፡፡ ችግሩን ወጥነት ባለው መልኩ ለመፍታት ከዛሬ ጀምሮ በደብረ ብርሃን ዞናል መናኸሪያ ዲጂታል የትኬት ሽያጭ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ዲጂታል የትኬት ሽያጩ መነሻቸውን ከደብረብርሃን ዞናል መናኸሪያ አድርገው ወደ ሁሉም አቅጣጫ ስምሪት በሚሰጣቸው ተሸከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ደጀኔ በቀለ በስልክ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ ይህ ዲጂታል የትኬት ሽያጭ ቀልጣፋ፣ ለአጠቃቀም ምቹ እና ሕዝቡን አግባብነት ከሌለው የታሪፍ ጭማሬ የሚታደግ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ወጣቶች ሥልጠና ተሰጥተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ደጀኔ ማብራሪያ አተገባበሩ ዘላቂነት እንዲኖረው እንሠራለን ነው ያሉት። ምንም ዓይነት የአፈጻጸም ክፍተት እንዳይኖርም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡ አገልግሎቱ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ተጓዦች ትኬትን በዲጂታል ሥርዓት ከቆረጡ በኋላ ተጨማሪ ክፍያ ሲጠየቁ ተስተውሏል፤ ይህንን ለማስቀረት ምን ታስቧል ስንል የጠየቅናቸው አቶ ደጀኔ ሕዝቡ ቅሬታ የሚያቀርብበት የጥሪ ማዕከል ጭምር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈጠር ችግርን በዘላቂነት ለማስቀረት ግን ሕዝቡ ተባባሪ እንዲኾን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘሃቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ለማሳካት መሰረት የምንጥልበት ነው” አቶ አደም ፋራህ
Next articleየምግብ እና ሥርዓተ ምግብ እቅዶችን ለማሳካት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።