“ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ለማሳካት መሰረት የምንጥልበት ነው” አቶ አደም ፋራህ

53

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዐላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚመከርበት መድረክ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት መካሄድ ጀምሯል። በምክክር መድረኩ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እንደ ሀገር ከተረጂነት እና ከልመና መላቀቅ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።

ከተረጅነት አስተሳሰብ ሳይላቀቁ ሉዐላዊነት እና ብሔራዊ ክብርን መጎናጸፍ እንደማይቻል እና ለዚህም በቁርጠኝነት መነሳት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ አቀናጅቶ በመጠቀም እና ለብልጽግና በማዋል የተረጂዎችን ቁጥር መቀነስ፣ ቀስ በቀስም ከተረጂነት መላቀቅ እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት።

ለዚህም ብቸኛው መፍትሔ ምርታማነትን በሁሉም ደረጃ ማሳደግ መቻል እንደኾነ ነው ያነሱት። እንደ ብልጽግና ፓርቲ የተረጂነት አስተሳሰብ እንደ ሀገር ሊፈጥረው የሚችለውን ቀውስ በውል በመረዳት ጉዳዩን ከሥር ከመሠረቱ ለመፍታት ሰፋፊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በተለይም ምርታማነትን አሳድጎ ዘላቂ እልባት ለማምጣት እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ የተደረጉ የሌማት ትሩፋትን የመሳሰሉ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እንዳስመዘገቡ ጠቅሰዋል። በላባችን እና በጥረታችን ከተረጂነት በመላቀቅ ብልጽግናን የማረጋገጥ ምዕራፍ መጀመር አለብን ነው ያሉት፡፡ ይህንን ማሳካትም ለሁለተኛው የአርበኝነት ምዕራፍ ጠንካራ መሰረት መጣል እንደኾነ ገልጸዋል።

በተረጂነት ሰበብ ሉዐላዊነታችንን ለሚገዳደሩ ጉዳዮች ተጋላጭ ላለመኾን ብሎም ብሔራዊ ክብርን ለማስጠበቅ እንደ ሀገር በእጃችን ላይ ያሉ ወረቶች በቂ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን አቀናጅቶ በመምራት ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
የተጀመሩ ሀገራዊ ንቅናቄዎችን በማስቀጠል፣ በተቀናጀ አቅም ማኅበረሰቡን ወደ ምርታማነት ማስገባት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የመጠባበቂያ እና የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ክምችትን በየደረጃው መያዝ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ለሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት የተረጂነት እሳቤን በዘላቂነት ለማጥፋት እንደ ሀገር የተለያዩ ተቋማትን በማካተት የተቋቋመው ኮሚቴ በትኩረት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው ከብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ሚንስትሮች፣ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ መሪዎች፣ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መሪዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ኾነዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በጋራ ሀገራዊ ውይይት እንጂ በግለሰቦች መግለጫ የሚወሰን አይደለም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleበደብረ ብርሃን ዞናል መናኸሪያ ዲጂታል የትኬት ሽያጭ ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡