“የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በጋራ ሀገራዊ ውይይት እንጂ በግለሰቦች መግለጫ የሚወሰን አይደለም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

67

አዲስ አበባ: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በጋራ ሀገራዊ ውይይት እንጂ በግለሰቦች መግለጫ የሚወሰን አለመኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፅዱ ኢትዮጵያ 20 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እስከ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም 36 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሀገሯ ለመመለስ በቀን ሦስት በረራዎች እያደረገች መኾኑን እና ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ በሳምንቱ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ 24 ለሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ሹመት መስጠታቸውን ተናግረዋል። ዲፕሎማቶቹ ሁሉም የውጭ ጉዳይ ባልደረቦች ሲሆኑ በዋናነት ብቃትን እና ኀላፊነትን የመወጣት አቅማቸው ተመዝኖ መኾኑን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ማይክ ሀመር ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውንም በመግለጫው ተነስቷል፡፡ የኢትዮ-ቻይና የንግድ ትርኢት መካሔዱ አንዱ የሳምንቱ የመስሪያ ቤቱ ተግባር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በንግድ ትርኢቱ ላይ 36 የቻይና ኩባንያዎች መሳተፋቸውንም ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ የንግድ ኤግዚቢሽን መካሄዱን አንስተዋል፡፡

በታንዛኒያ ለሚገነባው የኢፌዴሪ ኢምባሲ በዋና ከተማዋ ዶዶማ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከሀገሪቱ መንግሥት በተሰጠ 2 ነጥብ 5 ሔክታር መሬት ላይ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ በ6ኛው የሳውዲ ኢትዮጵያ የጋራ የሚኒስትሮች ውይይት ተሳትፈዋል። በዚህም የሁለቱን ሀገራት የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ለማጠናከር፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ የግብርና እና እንስሳት ንግድ እንዲሁም በማዕድን እና በኀይል አቅርቦት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ጠንካራ እንደመኾኑ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በስቴት ዲፓርትመነት ደረጃ ተነጋግረን በተረጋጋ ሁኔታ የሚወሰን እንጂ በግለሰብ ደረጃ እንደተፈለገው በየቦታው የሚሰጥ ሊሆን አይገባም የሚል አቋም ኢትዮጵያ መውሰዷን ተናገረዋል። በዚህም የአሜሪካው አምበሳደር በኢትዮጵያ የሰጡት መግለጫ ተገቢ አለመኾኑን አምባሳደር ነብዩ ተድላ አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ዘመናዊ የእናቶች እና ሕጻናት የህክምና መስጫ ሕንጻ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ፡፡
Next article“ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ለማሳካት መሰረት የምንጥልበት ነው” አቶ አደም ፋራህ