
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የእናቶች እና ሕጻናት የህክምና መስጫ ሕንጻ ማስገንባቱን በሰሜን ወሎ ዞን የመቄት ወረዳ የአልማ ዩኒሴፍ ፕሮጀክት አስታውቋል፡፡ ሕንጻው በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) እና ዩኒሴፍ በጋራ በመተባበር ነው የተገነባው።
የመቄት ወረዳ የአልማ ዩኒሴፍ ፕሮጀክት አሥተባባሪ አብርሃም ፈንታ ወረዳው በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት እና ዝርፊያ የደረሰበት መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ጤና ጣቢያዎች ለማኅበረሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው ብለዋል። የእናቶች እና ሕጻናትን ጤና በማሻሻልና ወደ ነበሩበት ለመመለስ በወረዳው በርካታ ተግባራቶችን እየፈጸመ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
በዋናነት በሐና መኳት ጤና ጣብያ ከዩኒሴፍ እና ከአልማ በተገኘ 5 ሚሊዮን 451 ሺህ 963 ብር ድጋፍ ዘመናዊ የእናቶች እና ሕጻናት የህክምና መስጫ ሕንጻ ገንብቶ ከነሙሉ ግብዓቱ ማስረከቡን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለጤና ባለሙያዋች የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዋች፣ የአንቡላንስ ጥገና፣ ነዳጅ፣ ክትባት፣ የጤና ጣቢያዋች ግብዓት የማሟላት እና መሰል ሥራዎችን በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የሐና መኳት ጤና ጣቢያ ኀላፊ ዳንኤል ደርበው የአማራ ልማት ማኅበር እና ዩኒሴፍ በጋራ ዘመናዊ ሕንጻ ገንብተው አስረክበውናል፤ ለዚህ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። የመቄት ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ይበልጣል ጌታ አልማ በዩኒሴፍ ድጋፍ በሐና መኳት ጤና ጣብያ በተጨማሪ በሰርኮ እና ጣጃ ጤና ጣቢያዎች በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ ይበል የሚያስብል ሰፋፊ ተግባራት እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የመቄት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ ደሳለው እንዳሉት የተሠራው ሕንጻ ለ6 ቀበሌዎች እና ለ25 ሺህ ሕዝብ ጥቅም የሚሠጥ ነው፡፡ ለተሠራው ሥራ ምሥጋና ማቅረባቸውን ከአልማ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!