
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ማድረሱ ይታወሳል፡፡ በተለይ ንፁሃን የጦርነቱ ሰለባ ኾነዋል፤ የግብርና ግብዓቶች በተገቢው መልኩ ለአርሶ አደሮች እንዳይደርሱ እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል፤ የግብርና ምርቶች እንደልብ ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱም ተገድበው ቆይተዋል፡፡
ሰዎችም ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር፡፡ ይህንን የሰላም መደፍረስ ችግር በመፍታት ሕዝቡ ማኅበራዊ ረፍት እንዲያገኝ ለማድረግ የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ሰላም የማስፈን ሥራዎችን በትኩረት እያከናወኑ መኾኑን የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ገልጿል፡፡
የቢሮው ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ባለፉት ጊዜያት ሰላምን ለማስፈን በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ለአሚኮ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ችግር ወጥቶ ነገሮችን በስክነት መመልከት ጀምሯል፡፡ የጦርነትን አውዳሚ ባሕሪይ በመገንዘብ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆሙ ለተገኘው አንጻራዊ የሰላም አየር አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የሰላም ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው አካባቢዎችም የልማት እና የኢንቨስትመንት እንቅስቀሴዎች በተሻለ መልኩ መነቃቃት አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡ ክልሉን ከጦርነት አዙሪት ለማውጣት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ ምክትል ቢሮ ኀላፊው የትኛውም ዓይነት ጥያቄ በአፈሙዝ እንደማይፈታ ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመገንዘብ ሰላማዊ አማራጮችን መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የሰላምን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉ ካለው ሕዝባዊ ኀላፊነት አንጻር የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም አረጋግጠዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ጦርነት የሚያደርሰውን ውድመት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡ በመኾኑም ጥያቄ ለማስመለስ የኃይል አማራጮችን መከተል ሕዝቡን ለተጨማሪ ጉዳት የሚዳርግ በመኾኑ ቆም ብሎ ማሰብ እና ወደ ጠረጴዛ ውይይት መቅረብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ኀላፊነት ተጥሎበታል ያሉት አቶ በሪሁን አስተማማኝ ሰላምን የማስፈን ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!