
ደሴ: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ “ሀገር በቀል ዕውቀት ለማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍቻ” በሚል መሪ ሀሳብ 7ኛውን ሀገር አቀፍ የቋንቋ እና ባሕል ዓውደ ጥናት እያካሄደ ነው። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለበርካታ ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፎች መኾናቸውን በመጥቀስ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ዐውቆ እና በተገቢው ሁኔታ አጥንቶ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል።
የቀድሞው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር) የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች የራሳቸውን ታሪክ ብቻ በመንገር የራሳቸውን ቋንቋ ብቻ ለማስተማሪያነት በመጠቀም የአፍሪካን ሀገር በቀል ዕውቀት እና ቋንቋ ለማጥፋት እና በራሳቸው ለመተካት መሥራታቸውን ተናግረዋል። በመኾኑም የራሳችንን ሀገር በቀል ዕውቀት ለመጠቀም እና ከቅኝ ገዢዎች ተፅዕኖ ለመላቀቅ ከትምህርት ሥርዓቱ እና ከሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ጀምሮ ሀገርኛ የኾኑ ዕውቀቶች ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በግጭት አፈታት፣ በሥነ ጥበብ እና ሙዚቃ፣ በተለያዩ ፈጠራ ሥራዎች የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በተግባር ማዋል ለችግሮቻችን መፍቻ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል። በአውደ ጥናቱ በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተጋበዙ አጥኚዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።
በዩኒቨርስቲው ግቢ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የቋንቋ እና ባሕል አውደ ጥናት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር)፣ የቀድሞው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር)፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!