
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር በቀል እውቀቶች በተሻለ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምሁራን በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ሊያደርጉባቸው እንደሚገባ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሀገር በቀል ዕውቀቶች ፎረም ምስረታ በአዳማ ከተማ ዛሬ አካሂዷል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ሁለንተናዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው የተበታተነውን አቅም በማቀናጀት መሥራት አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል። ከሌላ ሀገር ያልተዋስናቸውን እና የእኛ መገለጫዎች የኾኑ የፖለቲካ እና የአሥተዳደር ዘይቤዎችን ጨምሮ ባሕላዊ እውቀቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም የሰላም ግንባታችንን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል።
የፎረም ምስረታው በየዘርፉ በተናጠል በርካታ ሥራዎችን ሲሠሩ ለቆዩ ባለሙያዎች የጋራ አቅም እንደሚኾን ተናግረዋል። ከሁሉም በላይ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በተሻለ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምሁራን በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ሊያደርጉባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሚኒስቴሩ የባሕል እና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ዘመኑን የዋጀ ጠቀሜታ እንዲሰጡ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
በተለይም በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎባቸው በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ምሁራን የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት። ሀገር በቀል ዕውቀቶች የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ መገለጫ፣ የፍልስፍና እና የኪነ ጥበብ መሠረት በመኾናቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ፎረም መመሥረት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
በተመሰረተው ፎረም አስራ ሶስት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህም ሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም የሀገር በቀል ዕውቀትን በትምህርት ዘርፉ በማካተት አዲሱ ትውልድ እንዲረዳቸው ምሁራኑ ርብርብ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ ዘውዴ(ዶ.ር) ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለቴክኖሎጂው ዘመን ምቹ እንዲኾኑ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በአሥተዳደራዊ ሥራ፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ጥቅም ላይ ማዋል ፋይዳው የጎላ መኾኑንም አክለዋል።
እነዚህ ዕውቀቶች እንዳይዘነጉ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት በመጨመር አዲሱ ትውልድ አበልፅጎ እንዲጠቀምባቸው የማስገንዘብ ሥራ ይሠራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!