
ደሴ: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ታረቀኝ ትንታጉ (ዶ.ር) በውጭ ሀገር መቀመጫቸውን ካደረጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ዙርም ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የህክምና ቁሳቁስ ለጃማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ልዕለ ህክምና ካምፓስ ዲን ዶክተር መታደል አዳነ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለጃማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ማስረከባቸውን ገልጸው የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት እንደሚያሻሽለው ጠቁመዋል። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በወረዳው የሚገኙ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው የተናገሩት የጃማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ መሐመድ የሱፍ ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እያከናወነ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት እና የጤና ተቋማትን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!