
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርሶች ቀን ነገ በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ እንደሚከበር አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በኅዳር 2015 ባካሄደው 38ኛው ጉባዔ ግንቦት 15 የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀን እንዲኾን ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት ቀኑ በአሕጉር ደረጃ ለስምንተኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ነገ ግንቦት 15/2016 ዓ.ም “ትምህርት ለአፍሪካ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ጥበቃ” በሚል መሪ ሃሳብ በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ይከበራል። የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በሰጠው መግለጫ ቅርሶቻችን የአባቶቻችን የፈጠራ መዘክር ማኅተም ያረፈባቸው እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ጥንካሬ እና ጉልበት መገለጫ ናቸው ብሏል፡፡
በሀገራችን የባሕል እና የተፈጥሮ ቅርሶች መልማት እና መጠበቅ ከመስህብነት በዘለለ ለመልካም ገጽታ ግንባታ እና ለምጣኔ ሃብት እድገት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መኾኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ የቀኑ መከበር በቅርስ ዙሪያ የወጡ ዓለም አቀፍ አዋጆችን፣ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የቱሪዝም ፍስሰት እንዲጨምር፣ ቅርሶች ለአንድ ሀገር ዕድገት ያላቸውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ የሚረዳ ትውልድ ወይም ማኅበረሰብ እንዲኖር ያግዛል፡፡ ቅርስን መጠበቅ የሁለም ዜጋ ኀላፊነት መኾኑን ግንዛቤ ለመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ቀኑ በባሕላዊ እና በተፈጥሮ የመስህብ በረከቶች አጠባበቅ ሂደት ላይ በሚታዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ በመምከር የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ እንደሚያግዝም ተመላክቷል፡፡ የሀገሪቱን ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ሁለንተናዊ እሴታቸውን ከስጋት እና ከጉዳት በመከላከል እና በመጠበቅ ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለማዋል ይረዳል፡፡
በዚህም ሃብቶቹን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ትብብር ለማገዝ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1978 ዩኔስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የላቀ ሁለንተናዊ እሴትነት ያላቸውን ቅርሶች በመለየት ከመዘገባቸው 12 ቅርሶች መካከል ከአህጉሪቱ የተመረጡት ሦስት ቅርሶች ሲኾኑ ከእነዚህ መካከል ሀገራችን ሁለቱን በማስመዝገብ በአፍሪካ የቀዳሚነቱን ቦታ ወስዳለች፡፡
በአሁኑ ጊዜም ከ46 የአፍሪካ ሀገራት የተመረጡ 147 ቅርሶች በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ 11 ቅርሶችን በማስመዝገብ በክፍለ አህጉሩ የመሪነቱን ሚና መያዟን መግለጫው አመላክቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!