በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡

13

ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂደዋል፡፡ በምክክሩ ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም የሰላም አስፈላጊነትን ከአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ሕዝብ በላይ የሚረዳ የለም ብለዋል፡፡ ዋና አሥተዳዳሪው ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሰላም ሠርቶ የመለወጥ፣ ወልዶ የማሳደግ፣ ወጥቶ የመግባት፣ ዘርቶ የማፍራት እንዲሁም በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ እንዳለውም ነው ያብራሩት፡

ዋና አሥተዳዳሪው “ያለን አንጡራ ሃብት እየወደመ መተኪያ የሌለው የሰው ሕይዎትም እየጠፋ ነው” ብለዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ዋና አስተዳዳሪው ከአውዳሚው የእርሰ በእርሰ ግጭት በፍጥነት መውጣት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ወርቁ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ውይይቱ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት እያስከተሉ በመኾናቸው መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በጋራ የሕግ የበላይነትን ያሰከብራል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዲጂታል ልማት የሀገራችን የወደፊት የመልማት ዕድል እና የእያንዳንዱን ዜጋ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርሶች ቀን በጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ሊከበር ነው።