
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የዲጂታል ልማት የሀገራችን የወደፊት የመልማት ዕድል እና የእያንዳንዱን ዜጋ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል፡፡ ዛሬ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ላይ አትኩሮቱን ባደረገው ‘ስትራይድ ኢትዮጵያ’ ኤክስፖ 2024 ላይ ተገኝተን የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር ጠቃሚ ምክክሮችን አድርገናል ነው ያሉት።
አቶ ተመስገን እንዳሉት ወደ ዲጂታል ዓለም ሲገባ ጎታች አሠራሮችን እያስቀረ በአዲስ የሚተካ በመኾኑ ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ አደረጃጀቶችን በመቅረጽ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። ስለሆነም ከመንግሥት ጋር የግሉ ዘርፍ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የልማት አጋሮች በቅንጅት በልማቱ ውስጥ ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማስረፅ እና መላው ሕዝባችን ከዲጂታል ትሩፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካል ሀገራዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልእክት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!