
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እና የመሬት መረጃ አሥተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ሥራ (ካዳሥተር) እየሠራ ይገኛል። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት ባለፉት አሥር ወራት ከ1 ሚሊዮን 118 ሺህ 708 በላይ ማሳዎች ካርታ ተዘጋጅቶላቸዋል፤ የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሠርቶላቸዋል። ለ278 ሺህ 288 ባለይዞታዎች ደግሞ የ2ኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷል፡፡
2 ሺህ 139 ባለይዞታዎች የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን በዋስትናነት ተጠቅመው በአጠቃላይ ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል። በ130 ወረዳዎች የብሔራዊ የገጠር መሬት አሥተዳደር መረጃ ሥርዓትን መገንባት መቻሉንም ነው የገለጹት። በከተማ መሬት ምዝገባ፣ ከኢንቨስትመንት አገልግሎት፣ ከቀበሌ ማዕከላት እና ከገጠር መሬት አሥተዳደር እና ካዳስተር ዘርፍ ከ216 ሚሊዮን 653 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።
በክልሉ የሚገኙ የገጠር ከተሞችን ወደ ንዑስ እና መሪ ማዘጋጃ የማሸጋገር ሥራም እንደ ሀገርም የተሻለ መኾኑን ገልጸዋል። አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው የክልሉ አካባቢዎች የገጠር ኢንቨስትመንትን በአዲስ በመለየት፣ ውል በመስጠት፣ የውል ጊዜያቸው ያለቀባቸው ደግሞ መልሶ በማደስ የተሻለ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በከተሞች የካዳስተር ሥራው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ለልማት ተነሽዎች ካሳ አለመክፈል መሠረታዊ ችግር መኾኑን ገልጸዋል። እስከ አሁንም 7 ቢሊዮን ብር ለልማት ተነሽዎች ካሳ አለመከፈሉን በማሳያነት አንስተዋል። የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን ይበልጥ ማዘመን፣ የገጠር እና የከተማ የካዳስተር ሥራውን ማጠናከር፣ ለልማት ተነሽዎች የካሳ ክፍያ መፈጸም በቀጣይ ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ኾነው ተቀምጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!