
እንጅባራ: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መምሪያው የ2016 በጀት ዓመት የባለፉት 10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ 60 ቀናት ዕቅዶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በእንጅባራ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2016 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ ባለፉት 10 ወራት መሠብሠብ የተቻለው 931 ሚሊዮን 302ሺህ 905 ብር ነው። ይህም ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ 32 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ፈጠነ ጥላሁን ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ቀደም ባሉት ዓመታት ከዕቅድ በላይ ገቢ የመሠብሠብ ልምድ ያለው ቢኾንም በክልሉ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ መሸፈን እንዳልተቻለ ተናግረዋል። የሰላም ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የግብር ውሳኔዎችን በማሳወቅ ገቢ የመሠብሠብ ሥራ መጀመሩንም ኀላፊው ገልጸዋል።
በቀሪ 60 ቀናት ከቁርጥ ግብር አወሳሰን ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ቅሬታዎች ፈጣን ውሳኔ በመስጠት የታቀደውን ገቢ አሟጦ ለመሠብሠብ ጥረት እንደሚደረግም መምሪያ ኀላፊው አንስተዋል። በግምገማ መድረኩ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የኅብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ፍላጎቶችን ለማሟላት ገቢን አሟጦ መሠብሠብ ለነገ የሚባል ተግባር አለመኾኑን ገልጸዋል። በቀሪ ጊዜያት ለሚከናወኑ የገቢ አሠባሠብ ሥራዎች ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!