“ቴክኖሎጂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለውን አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ በአግባቡ ትጠቀምበታለች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

50

አዲስ አበባ: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ የፓናል ውይይት እየተካሔደ ነው። የፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራ የእስካሁኑ ሂደት ፈተናዎች እና የቀጣይ እቅዶች ላይ መሰረት ያደረገ ነው።

በመድረኩ ተገኝተው የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኗን ተናግረዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂ ለሀገር ልማት የሚያመጣውን ቱሩፋት በተመለከተ ነው የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት። በመድረኩ በማንኛውም የመንግሥት አገልግሎት ላይ ያለውን ብልሹ አሠራር ለማስተካከል ቴክኖሎጂ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ማኅበራዊ ተሳትፎ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥሩ አስተዋጽኦ እንዳለውም አብራርተዋል። ተደራሽነትን ለማሳደግ እና ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ሚና አለውም ብለዋል። ወጣቶች ለቴክኖሎጂ ያላቸውን መሰጠት በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ መንግሥት ከያዛቸው አምስት የትኩረት ነጥቦች ውስጥ አንደኛው ቴክኖሎጂ መኾኑን አንስተዋል። ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ስለማድረጉ ነው ያስገነዘቡት፡፡

“ቴክኖሎጂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለውን አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ በአግባቡ ትጠቀምበታለች” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በ2025 መንግሥት ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሰጠው ትኩረት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት እንዳለው ማሳያ ስለመኾኑም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፓስፖርት አሁን ላይ ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ እየተሰጠ ነው” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት
Next articleባለፉት 10 ወራት ከ931 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።