
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተያዘው ዓመት ፓስፖርት ጠይቀው ይጠባበቁ ከነበሩ ዜጎች መካከል ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑት መስጠት መቻሉን አገልግሎቱ ገልጿል። የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የፓስፖርት አገልግሎት አንዱ እና ዋነኛው ነው። ይሁን እንጂ የፓስፖርት አሰጣጥን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይነሳሉ።
በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሚነሱ ቅሬታዎች አንዱ መጉላላት ነው የሚለው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ያሬድ መንግሥቱ፤ እርሱ ራሱም ላላገኘው አገልግሎት ሁለት ቀን በሰልፍ መጉላላቱን ገልጿል። አገልግሎት ፈልጎ በፍጥነት ማግኘት ከባድ እንደሆነ የሚናገሩት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ መዓዛ ቅዱስ በአንድ ቀን ጉዳይን ማከናወን ካለመቻሉም በላይ በሰልፍ ጊዜን አባክኖ አገልግሎቱን ሳያገኙ መመለስም እንዳለ ነው የሚናገሩት።
በተለይ ደግሞ አገልግሎት ለማግኘት መጠበቅ ግዴታ ሲሆንም፤ ለአዛውንቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ሳይቀር ምቹ የወረፋ መጠበቂያ ቦታ አለመኖሩ የአገልግሎት አሰጣጡ ሌላው ክፍተት መሆኑን ነው ተገልጋዮች የተናገሩት። በተገልጋዮች የተነሱትን ቅሬታዎች ጨምሮ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር ስለመኖሩ የሚያምኑት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ኬላዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ጌታቸው ወንድሙ ተጠቃሚውም ጋር ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል።
አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ወረፋ መጠበቅ ያስፈለገው በዋናነት በተቋሙ በኩል ባለው የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ውስንነት ምክንያት ነው ብለዋል። በተገልጋዮች በኩልም የቀጠሮ ቀናቸውን አለማክበር ወይም አሳልፎ መምጣት ይስተዋላል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። በተቋሙ በኩል በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ የሚታዩ ውስንነቶችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን እና የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ችግርን ለመፍታትም እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሙሉ ለሙሉ ችግሮች እስኪፈቱ በጊዜያዊነት በፈረቃ እስከ ምሽት ድረስ በመሥራት ችግሮችን ለማቅለል እየተሞከረ መሆኑን፣ በተጨማሪም ፓስፖርት በሀገር ውስጥ እንዲታተም የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል። በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሂደት ሙሉ በሙሉ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን እና በተያዘው ዓመት ፓስፖርት ጠይቀው ይጠባበቁ ከነበሩ ዜጎች መካከል ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑት መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ፓስፖርት ለመውሰድ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስድ እንደነበር የሚናገሩት ዳሬክተሩ፤ አሁን ላይ ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ እየተሰጠ እንደሚገኝም መግለጻቸውንም ኢቢሲ ዘግቧል። ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረው ቴክኖሎጂ ችግሮች እንዲባባሱ ያደረገ እንደነበር ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ ሲገቡ እና የሰው ኃይል እጥረቱ ሲቀረፍ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚነሱ ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፉ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!