“ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙኀን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ

27

የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በምክክር በመፍታት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የመገናኛ ብዙኀን ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ። ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ሚዲያ ለኢትዮጵያውያን ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር፤ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል። የምክክር ሂደቱ አሁን ላይ በ10 ክልሎች እና በ2 የከተማ አሥተዳደሮች 17 ሺህ 210 ተወካዮች የተመረጡ ሲሆን የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በምክክር በመፍታት ሰላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙኀን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በእስካሁኑ ሂደት የመገናኛ ብዙኀን ለነበራቸው አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም የላቀ ሚናቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ ለኮሚሽኑ ጥረት መሳካት የመገናኛ ብዙኀን ሚና ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል። በመሆኑም ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የመገናኛ ብዙኀን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

ኢዜአ እንደዘገበው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱንም በቅርቡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሄድ መሆኑ ታውቋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አስካሁን ከ6ሺህ 215 በላይ ተባባሪ አካላት ጋር መሥራቱም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖን ጎበኙ።
Next article“ፓስፖርት አሁን ላይ ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ እየተሰጠ ነው” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት