
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዋጋ ግሽበትን ከነበረበት ወደ በ23 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡ የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመላክተው የዋጋ ንረት በተለይም ለምግብ ፍጆታነት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች በየጊዜው እየጨመሩ በመሆኑ በመንግሥት በኩል ቢያንስ እየጨመሩበት ያለውን መጠን ለመቀነስ እየተሞከረ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መንግሥት ነዳጅና ማዳበሪያ ላይ የተለያዩ ድጎማዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፣ የውጭ ዕዳዎች አከፋፈል፣ የዓለም የፖለቲካ አቋም መለዋወጥ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተግዳሮቶች ከፍተኛ በመሆኑ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የታቀደውን ግብ ማሳካት አለመቻሉን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር በማበረታታት ትልቅ ስራ እየተሰራ ቢሆንም በበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ የዘርፎች ተወዳዳሪነትና ምርታማነት አሁንም ትልቅ ሥራ የሚፈልግ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ በቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትን እየፈጠረ በሚገኘው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የጨበራ ጩርጩራ፣ ዝሆን ዳና ሎጅ፣ የወንጪ ቱሪዝም መዳረሻ ፣በቅርብ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ የሚጠበቀው ጎርጎራ ሪዞርትን እንደዚሁ ማንሳት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማቶች፣ የመንግሥት የልማት ድርጀቶች እና ሌሎች አስፈፃሚዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተሠሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ ልማትን የሚያሳልጡ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንን ጨምሮ በዚ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!