
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በዕውቀት እና ክህሎት የበለጸገ እና ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከታቀደው ከ1 ሚሊዮን 232 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በዕቅድ ተይዞ ነበር። የሥራ ዕድል ፈጠራው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች፣ በተቋማት እና በውጭ ሀገር ብሩህ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ነበር የታቀደው።
በበጀት ዓመቱ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ተብሎ በዕቅድ ከተቀመጠው ውስጥ በ10 ወሩ ለ609 ሺህ (50 በመቶ) ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተገልጿል። በተለይም ደግሞ ባለፉት አራት ወራት በክልሉ በሚገኙ ስምንት ሪጅኦፖሊታንት ከተሞች በተሠራው ሥራ 400 ሺህ የሚጠጋ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። ከተሞቹ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ እና 350 ሚሊዮን ብር ማቅረባቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።
የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ውስጥ 62 ሺህ የሚኾኑት በውጭ ሀገራት የተፈጠረላቸው ናቸው። ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ያለውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ለማዘመን ስድስት ሲስተሞችን በማበልጸግ የዲጅታላይዝ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ይህም የሐሰት ሪፖርትን፣ ሐሰተኛ መረጃን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮችን እንደሚቀርፍ አንስተዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት እንደጀመረ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራ ማነቆ የኾኑ መመሪያዎችንም የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የቢሮው ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና በሥራ ላይ ያሉትንም ለመደገፍ እንቅፋት ማጋጠሙን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!