
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እምቅ የመልማት አቅም፣ አምራች የሰው ኃይል እና ምቹ የሥራ ከባቢ ያላት ኢትዮጵያ ለዘመናት ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት መሠረቷ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ትከሻ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የቆየ ነው፡፡ ከልማድ ፈጽሞ ያልተላቀቀው እና ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ግብርና መፃዒውን እድገት መቋቋም ቀርቶ አሁናዊውን የሀገሪቷን እድገት እና ፍላጎት የማሟላት አቅሙ ውስን ነው ይባላል፡፡ በመኾኑም በጊዜ ሂደት እውን የሚኾን እና መፃዒውን እድገት የሚቋቋም ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር እንደሚያስፈልጋት እሙን ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በጊዜ ሂደት ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለምታደርገው ሽግግር ተስፋ ከጣለችባቸው ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች የላቀውን ሚና ይጫዎታሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለዚህም ሲባል በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የተቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሽግግሩን በማምረት አቅም፣ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በተወዳዳሪነት ለመምራት እንዲቻል ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በተለያዩ አካባቢዎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በሀገሪቷ የሚገኙት እና 38 የሚደርሱት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች የተቋቋሙ ናቸው፡፡ መንግሥት ብቻ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም ዘርፉን ለመደገፍ ጥረት ተደርጓል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መቋቋም ዓላማዎቹ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ማመንጨት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ማድረግ ነው የሚሉት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት አማካሪው ወረታው ሞትባይኖር ናቸው፡፡ ላለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ያሳዩት እድገት የተቀመጠላቸውን ዓላማ ለማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ ነበርም ይላሉ፡፡
በተቋቋሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ የውጭ ባለሃብቶች እና ውስን የሀገር ውስጥ አምራቾች ገብተው ማምረት ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩት ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ክስተቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ህልውና ላይ ፈተናዎችን ደቅነዋል ያሉን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ናታኒየ ካሳ ናቸው፡፡ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ኢትዮጵያ ከአግዋ የገበያ ተጠቃሚነት መታገድ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ቀጣይነት ላይ አደጋ የፈጠሩ ልዩ ክስተቶች ነበሩ ይላሉ፡፡
አዋጅ ቁጥር 886/2015 እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው 417/2017 መመሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ለማቋቋም፣ ለመምራት እና ለመቆጣጠር የወጡ ማስፈጸሚያዎች ናቸው፡፡ በወጣው አዋጅ እና መመሪያ መሠረት ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለውጭ ባለሃብቶች ቅድሚያ የሚሰጡ ከመኾናቸው ባሻገር የሚያመርቷቸው ምርቶች ለዓለም አቀፍ ገበያ ብቻ እንዲቀርቡ ትኩረት የሚሰጡ ናቸው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከአግዋ ልዩ ተጠቃሚነት መታገድ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ገብተው የሚያለሙ የውጭ ባለሃብቶችን ቀጣይነት አደጋ ውስጥ ጣሉት፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ ሳይታሰብ የተፈጠረውን ክስተት ተቋቁመው የሚያመርቱ ውስን የውጭ ባለሃብቶች አሁንም ድረስ ቢኖሩም በርካታ ባለሃብቶች ግን ሠራተኞቻቸውን በትነው እና ፓርኮቹን ለቅቀው እንዲወጡ አስገድዷል ይላሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተለይም የኮሮና ቫይረስ የፈጠረውን ክፍተት ተከትሎ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አምራች ድርጅቶች ከዓመታዊ ምርታቸው 50 በመቶውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ እና ለአራት ወራት ብቻ የሚቆይ መመሪያ አውጥቶ ነበር፡፡ የኢንቨስትመንት አማካሪው እንደሚሉት ለአራት ወራት የቆየው ልዩ መመሪያ አሁን ለወጣው ልዩ የኢኮኖሚክ ዞን መመሪያ መነሻ ኾኗል ይላሉ፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል የወጣው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መመሪያ በአንድ ጀምበር የወጣ አይደለም የሚሉት አቶ ናታኒየ የመመሪያው ዓላማ በዋናነት በፓርኮቹ ውስጥ የሚያመርቱ ድርጅቶች 50 በመቶ ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ዕድል የሰጠ ነው፡፡ ከአግዋ የገበያ ዕድል መታገድን ተከትሎ የተቀዛቀዘውን የፓርኮቹን የማምረት ክፍተት ለመሙላት ከማገዙም በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ፓርኮቹ እንዲገቡ፣ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እና በቀጣይ ለሚፈጠሩ መሰል ክስተቶች የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያመላክት የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡
እንደ ኢንቨስትመንት አማካሪው ገለጻ በቅርቡ የወጣው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መመሪያ በርካታ ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳዎች አሉት፡፡ እስካሁን ፓርኮቹን ለቅቀው ያልወጡ አልሚ ድርጅቶች እንዲቀጥሉ እና ሌሎች የውጭ ባለሃብቶችም እንዲሳቡ ያግዛል፡፡ የሀገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች እንዲገቡ እና ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ከማገዙም በላይ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም በሀገሪቱ የተረጋጋ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ የሚጫዎተው ሚና የላቀ ነው፡፡
በመጨረሻም አማካሪው የወጣው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መመሪያ እንዲሳካ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተጨማሪ ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ መንግሥት እና አልሚ ባለሃብቶች ማገዝ እና የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!