
መነሻውን ከሰሜን ወሎ ዞን ላልይበላ ከተማ አድርጎ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ይጓዝ የነበረ አውቶብስ ወደ ጥልቅ ገደል በመግባቱ የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል።
የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ነፃነት አበራ ለአብመድ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ መጋቢት 09/2012 ዓ.ም ከሰዓት 11:30 አካባቢ ነው።
እንደ ኮማንደር ነፃነት መረጃ ኮድ 3 አማ 02180 የሆነ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ 023 ቀበሌ ልዩ ስሙ አጥቢያ በተባለ ቦታ ላይ ወደ ኋላ ተንሸራትቶ ነው አደጋው የደረሰው።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም በአደጋው የ10 ሰዎች (የ5 ወንድ እና የ5 ሴት) ሕይወት ሲያልፍ 14 ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በአደጋው ጉዳት ያልደረሰባቸው መንገደኞች መኖራቸውንም የተናገሩት ኮማንደር ነፃነት ጉዳዩን በዝርዝር የሚያጣራ ቡድን ወደ ቦታው ማምራቱንም ገልጸዋል።
የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም ለሕክምና ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸው ታውቋል።
በአጠቃላይ በተሽከርካሪው ውስጥ ስንት ተሳፋሪዎች እንደነበሩ፣ ስንት ሰዎች ከአደጋው እንደተረፉና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ የምርመራ ቡድኑ ካጣራ በኋላ መረጃ እንደሚቀርብ ነው የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ነፃነት የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም-ከደሴ