“ከ276 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደዋል” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ

67

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት የ10 ወር ዕቅድ አፈጻጸም እና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ውይይት አካሂደዋል። በ2016 በጀት ዓመት 3 ሺህ 640 አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ገብተው ያለማሉ ተብሎ በዕቅድ ተይዞ ነበር። ከዚህ ውስጥ ከ276 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 2 ሺህ 10 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ገልጸዋል። ከ360 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉ ናቸው።

ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ለማስገባት ባለፉት ሁለት ዓመታት በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ትኩረት ተደርጎ ሢሠራ ቆይቷል። በዚህ በጀት ዓመትም ችግር ባለባቸው 11 ሪጅኦ ፖሊታንት ከተሞች፣ 48 መካከለኛ ከተሞች እና የወረዳ ማዕከላት ከ5 ሺህ 600 በላይ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት ውይይት መደረጉን አንስተዋል።

65 በኀይል አቅርቦት ምክንያት ምርት አቁመው የነበሩ አዳዲስ መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ተደርጓል። በዓመቱ መጨረሻ 125 አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል። ባለፉት ወራት በክልሉ ያጋጠመው የሰላም ችግር የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ፣ ጥሬ እቃ ለማስገባት እና ሠራተኛው በሙሉ አቅሙ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ፈታኝ አድርጎታል።

ከዚህም በተጨማሪ መሬት በአግባቡ የማስተላለፍ፣ ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ወደ ሥራ የማስገባት ችግሮችም መኖራቸውን ገልጸዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ልክ አለማምረትም ሌላው ችግር እንደኾነ ተነስቷል። የአምራች ኢንዱስትሪው አሁን ከአለበት መቀዛቀዝ እንዲነቃቃ ባለድርሻ አካላት ለሰላም ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ !
Next articleበቅርቡ የወጣው ልዩ የኢኮኖሚክ ዞን መመሪያ ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ ምን ይኾን?