“ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎችን ለመለየት ውይይት እየተደረገ ነው” አቶ አደም ፋራህ

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይነት ምክክር የሚደረግባቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ለመወሰን የምክክር መድረክ እያካሄዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ባወያዩበት ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት እና ችግሮችን ለመፍታት ተከታታይ ውይይቶች እንዲደረጉ እና አጀንዳዎች እንዲለዩ አቅጣጫ አስቀምጠው ነበር።

በዚሁ መሠረት በዛሬው ዕለት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አደም ፋራህ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር አጀንዳዎችን ለመለየት እና የምክክር ሂደቱን ለመወሰን እየተወያዩ ነው። በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የመድረኩ ዓላማ መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር፣ ከተቋማት እና ከክልሎች ጋር በሚደረጉ ውይይቶች የሚቀርቡ አጀንዳዎችን መለየት እና ምክክር የሚደረግባቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለመወሰን ነው። አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት ውይይቱ በመንግሥት እና በፓርቲዎች መካከል የትብብር ባሕልን ለማጠናከር እና ጤናማ የፖለቲካ ፉክክርን ለመትከል የሚያስችል ነው።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲደግፉ ምቹ ምህዳር ይፈጥራልም ብለዋል። በቀጣይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ሀገራዊ የኾኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ የስትራቴጂ ጉዳዮችን መለየት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎችን ለመለየት ዛሬ የመጀመሪያው ውይይት እየተደረገ ነው ያሉት አቶ አደም በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዋናውን የዝናብ ወቅት ምርት ሳናስተጓጉል የበጋ ስንዴ ልማት ጥረታችንን ለማስፋፋት ችለናል። የዛሬው ምልከታ የሥራዎችን ቀጣይነት የተመለከትንበት ነበር። ግብርና ጠንካራ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል። በሰብል የምንሸፍነው የመሬታችን ይዞታም ቀስ በቀስ በመጨመር ላይ ይገኛል።” ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
Next articleየቅጥር ማስታወቂያ !