
እንጅባራ: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 የትምህርት ዘመን ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው የአዊ ብሔረሰብ አሳስቧል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2016 የትምህርት ዘመን ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች አሥተዳደር እና በቀሪ ሥራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ከመጪው ሰኔ 4/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሚሰጡ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል። የፈተና መስጫ ማዕከላትን ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ተማሪዎችን ለፈተና ማዘጋጀት እና ትራንፖርት ማመቻቸት ከወዲሁ ትኩረት የተደረገባቸው ሥራዎች መኾናቸውንም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታው አለሙ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የግል ተፈታኞችን ጨምሮ ከ22 ሺህ በላይ የሚኾኑ ተማሪዎች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎች በቀጣይ ወራት ለሚሰጡ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን የሚወስዱ የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው ብለዋል፡፡
ትምህርት በሚሰጥባቸው በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በሥነ ልቦና ማዘጋጀት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶችን መሸፈን እና ተማሪዎችን ለፈተና እንዲዘጋጁ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል። በቀሪ ወራት በተለያዩ ምክንያቶች የባከነውን ትምህርት ማካካስ እና ተማሪዎችን ለፈተና የማዘጋጀት ሥራ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መምሪያ ኀላፊው አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የመጽሐፍ አቅርቦት መጓተት እና የፀጥታ ችግሮች በትምህርት ሥራው ላይ ከፍተኛ ችግር ቢፈጥሩም ችግሮችን ተቋቁመው ተማሪዎችን ለፈተና እያዘጋጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት በማይሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎችን በተመለከተ በቀጣይ ወራት የሰላም ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ እንደሚቀመጥም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!