
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቱሪዝም ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡ በግምገማው ላይ ሚኒስቴሩ ባቀረበው ሪፖርት እንዳለው በመቅደላ ጦርነት ከሀገር ተዘርፈው የተወሰዱ ሰባት ቅርሶች ከእንግሊዝ ሀገር እንዲመለሱ መደረጉ ተገልጿል።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እና ሌሎች የሚኒስትሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች 7 ሺህ 150 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መመዝገባቸውም ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ 500 ቅርሶች በተሟላ መረጃ በዲጂታል ዳታ ቤዝ መሰነዱን ተከትሎ 1 ሺህ 196 ቋሚ ቅርሶች መመዝገባቸውን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ በመንግሥት እና በግል ሽርክና በቅንጅት የሚሠሩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች በመኖራቸው የግሉን ባለሃብት ለመደገፍ የመሬት ካርታ ከማቅረብ በተጨማሪ ተሸከርካሪዎችን እና ለኢንቨስትመንቱ የሚያገለግሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ ሰፊ ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።
በሀገሪቱ በአብዛኛው የቱሪስት መስህቦች ያሉበት መዳረሻ መሠረተ ልማት እንዲኖር ከግሉ ባለሃብት፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሌሎችም ጋር እየተሠራ መኾኑም ነው የተብራራው፡፡ ከኢትዮጵያ ኤርፖርት እና ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር በቅርበት እየተሠራ መኾኑ ለአብነት ተነስቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በብሔራዊ ልማት ከሚሠራው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባሻገር ለቱሪሰቶች ማራኪ እና ውብ የጉብኝት ቦታ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑ ነው የተገለጸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!