
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) እና የአማራ ክልል የአካባቢ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን በአካባቢ ጥበቃ ላይ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራርመዋል።
የአማራ ክልል የአካባቢ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን አለምነህ ተቋማቸው ከአሚኮ ጋር በአካባቢ ጥበቃ ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠልም የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለተወሰነ ጊዜ እና አካላት ብቻ የሚሰጥ ሳይኾን የሁሉም ኀላፊነት መኾኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋሁን ተደራሽ ሚዲያ ጋር ተባብሮ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል። ስምምነቱ በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ የኅብረተሰብ ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ መኾኑን ጠቅሰዋል። አሚኮ ያለውን ሰፊ ተደራሽነት በመጠቀም የአካባቢ ጥበቃ የግንዛቤ ፈጠራን የማሳደግ ሥራ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ስምምነቱ ክልሉ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ጉልህ ሥራ በመሥራት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካል መኾኑንም አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል። የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥየ አሚኮ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በርካታ ሥራዎች መሥራቱን አስታውሰው ከዚህ በፊትም በጋራ ለመሥራት ስምምነት መደረጉን ጠቅሰዋል።
“አሚኮ ለኅብረተሰብ ለውጥ እንደመትጋቱ ዜጎች ምቹ የኾነ የመኖሪያ እና የሥራ ከባቢ እንዲኖራቸው በሙያችን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን” ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው። በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ አሚኮ የጀመራቸው ሥራዎች መኖራቸውን እና ሥምምነቱም ጅምሮቹን አጠናክሮ በመቀጠል ውጤታማ ለማድረግ መኾኑን ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ውጤታማ መኾን ተጠቃሚ የሚያደርገው ማኅበረሰቡን ነው፤ ኅብረተሰቡ ሲያግዝም ውጤቱን እና ተጠቃሚነቱን ስለሚያጎላው በትኩረት እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!