
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
በሰሜን ሸዋ ዞን በሰላም እና በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ባለፉት ጊዜያት ሰላምን ለማስፈን የተከናወኑ ተግባራትን በመፈተሽ የቀጣይ ሥራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው። የኮማንዶ እና የአየር ወለድ እዝ ምክትል አዛዥ እና የሰሜን ሸዋ ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀኔራል አበባው ሰይድ በሰጡት ሃሳብ ባለፉት ጊዜያት በተወሰደው የሕግ ማስከበር ተግባር በርካታ ለውጥ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
በዋናነት ተገድቦ የነበረው የሕዝብ እንቅስቃሴ መሻሻሉ፣ እገታዎች መቀነሳቸው እንዲሁም የልማት ሥራዎች እንዲሳለጡ ምቹ ሁኔታ መፈጠር መቻሉን ጠቅሰዋል። “ለአርሶ አደሮች ለማድረስ ሲጓጓዝ የነበረን ግብዓት ጽንፈኛው ኀይል እየዘረፈ በከፍተኛ ዋጋ ይቸበቸብ ነበር” ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል አበባው ሰይድ አሁን ላይ ሠራዊቱ እስከ ቀበሌ ማዕከላት ድረስ አጅቦ በማድረስ በአግባቡ ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የፀጥታ ሁኔታ መሻሻል በታየባቸው አካባቢዎች የልማት ሥራዎች እየተነቃቁ መኾኑን በማመላከትም ሰላምን የማስፈን ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በውይይቱ የወረዳ አሥተዳደር አካላት፣ የዞን የሥራ ኀላፊዎች እና የፀጥታ አካላት ተሳታፊ ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!