
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምርት እና አገልግሎታቸውን ለመሸጥ ሕዝብ በሚሠበሠብባቸው ቦታዎች በድምጽ ማጉያ የሚያስተዋውቁ ሰዎችን ማየት የተለመደ ነው። የጸረ ተባይ መድኃኒቶች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የአልባሳት፣ የሕክም አገልግሎት እና የእርዳታ ጥሪ በየቦታው በድምጽ ማጉያ ከሚተዋወቁት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
በመንቀሳቀስም ኾነ በቋሚ ቦታ የሸማችን ቀልብ በመሳብ ምርትና አገልግሎትን ለመሸጥ የሚሠራ ማስታወቂያ በአካባቢው በቋሚነት ለሚሠሩ እና ለሚኖሩ ብቻ ሳይኾን አልፎ ሂያጅንም የሚያሰጨንቅ ድምጽ ነው። በአካባቢው ከሚኖረው የትራፊክ መጨናነቅ፣ የተሽከርካሪ ድምጽ፣ ከመቸኮል እና ከመሰረቅ ስጋት ጋር ተደማምሮ ለአደጋም ያጋልጣል።
ሁሉሀገርሽ ደባልቄ የጸረ ተባይ መድኃኒት ትሸጣለች። ለዚህም የተቀረጸ ማስታወቂያ ያለማቋረጥ በድምጽ ማጉያ ከፍ አድርጋ ትለቃለች። ”ሌሎችም እንደኔ የሚሸጡ ስላሉ ገዢን ለመሳብ ነው” ብላለች። ሳሚ ይበልጣል ደግሞ ቴሌቪዥን በሎተሪ ለመሸጥ በሙዚቃ የታጀበ ቅስቀሳ ያደርጋል።
ሁሉሀገርሽም ኾነች ሳሚ እየተዘዋወሩ መሥራትን እንጂ የሚለቁት ድምጽ ሕዝብ የሚረብሽ ነው ብለው አያምኑም። በሕግ መከልከሉንም አያውቁም።
አቶ ውቤ መንጌ የባንክ ጥበቃ ሠራተኛ ናቸው። በሥራ ቦታቸው አካባቢ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ላይ በድምጽ ማጉያ የሚለቀቅ ድምጽ ሲጨመርበት ”አቅል ያሳጣል” ነው ያሉት። ”ሥራየን ካልለቀቅኩ በስተቀር በዚህ ቀን አርፋለሁ የማልለውና ጆሮ የሚበሳ የድምጽ ብክለት ነው የጣለብኝ” ብለዋል።
አቶ በላይነው አሻግሬ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በንግድ ሕግ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ10 ዓመታት የሕግ መምህር ኾነው ያገለገሉ ሲኾን አሁን ደግሞ የፌዴራል ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው። እንደ አፈር፣ አየርና የምግብ ብክለት ሁሉ የድምጽ ብክለትም መኖሩን እና ይህን ለመከላከልም ሕግ እንዳለው ጠበቃና የሕግ አማካሪ በላይነው ይገልጻሉ። የሚለቀቁ ከፍተኛ ድምጾች የሕግ ገደብ እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት። የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/1995 ድንጋጌ በካይ ነገሮች ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ወይም ንዝረት አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በሕግ እና በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠው የድምጽ ጩኸት መጠን ፈቃድ፡-
👉 ለመኖሪያ አካባቢ፦ በቀን 45 ዴሲ ቢል ሲኾን በማታ 55 ዴሲ ቢል
👉 ለንግድ አካባቢ፦ በቀን 55 ዴሲ ቢል፣ በማታ 65 ዴሲ ቢል
👉 ለኢንዱስትሪ መንደር፦ በቀን 70 ዴሲ ቢል ሲሆን በማታ ደግሞ 75 ዴሲ ቢል መኾኑን እና ከዚህ ከጨመረ የድምጽ ብክለት እንደኾነ የሕግ ባለሙያው ገልጸዋል።
ማንኛውም ሰው ንጹህና ጤናማ በኾነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳ’ለው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44 ላይ መደንገጉን የጠቀሱት ጠበቃና የሕግ አማካሪ በላይነው መብቱ ከድምጽ ብክለት ነጻ መኾንንም እንደሚያካትት ጠቅሰዋል። የከተማ አሥተዳደሮችም ችግሩን የመከላከል እና የማስወገድ ኀላፊነት አለባቸው። ለዚህም መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ከተጣሉበት ግዴታዎች ውስጥም የሚረብሽ፣ እረፍት የሚነሳና ለጤና መታወክ የሚዳርግን ድምጽ ማስወገድን የሚያካትተውን ለዜጎች ጤናማና ንጹህ አካባቢ የመፍጠርን የአንቀጽ 92 ድንጋጌን የሕግ ባለሙያ በላይነው ይጠቅሳሉ።
በፍትሐ ብሔር ሕጉ የአካባቢ ብክለት አዋጅ 300/1995፣ እና የአካባቢ ተጽዕኖ አዋጅ 299/1995 የድምጽ ብክለትን በይነዋል። የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2004 በአንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 3 በማስታወቂያ ሰበብ የድምጽ ማጉያ በመጠቀም ከተፈቀደው የድምጽ መጠን በላይ ማስጮህና አካባቢን መበከል ሕገ ወጥ መኾኑን እንደሚደነግግ የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል።
ሕግ ማስከበር ያለባቸው የመንግሥት አካላት ሕገ ወጥ ተግባራትን ቀድመው ባለመከላከላቸው ወይም ከጅምሩ ባለማረማቸው የማኅበረሰቡን ጤናማ መስተጋብር የሚጎዱ እና ሕገ ወጥነትን የሚያበረታቱ ተግባራት ባሕል እየኾኑ ነው። ሕግን ያከብር የነበረ ዜጋም ‘ካልተከለከለማ…’ በሚል ሕገ ወጥነትን ይጀምራል።
በሕገ ወጥ ጩኸቱ የሚረበሸው ማኅበረሰብም የድምጽ ብክለቱ እንዲቆምለት ለፍርድ ቤት በማመልከት ደኅንነቱን ሊጠብቅ እንደሚችል ነው የሕግ ባለሙያው ያመላከቱት። በሕግ ከተፈቀደው የድምጽ መጠን በላይ የሚያስጮህ አካል በአካባቢ ብክለት አዋጅ 300/1995 አንቀጽ 16 ላይ የወንጀልም የፍትሐ ብሔርም ተጠያቂነት እንዳለበት ተጠቅሷል። ከአንድ እስከ አስር ሺህ ብር መቀጮና ከአንድ እስከ አሥር ዓመት እስራት ያስከትላል።
ለዚህ ተግባር የዋለ ንብረትም ሊወረስ ይችላል፤ ካሳም ሊጠየቅበት ይችላል። ጥፋቱን የፈጸመው የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት ከኾነ ደግሞ ድርጅቱ ከአምስት እስከ ሃያ አምስት ሺ ብር መቀጮ እና የድርጅቱ ኀላፊ ደግሞ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ድረስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል። አሁን አሁን የፋብሪካ እና የግብርና ምርቶችን እየተዘዋወሩ ለመሸጥ ሲባል በከተሞች በከፍተኛ ድምጽ ማስታወቂያ ይሠራል።
በፍጥነት ካልተስተካከለም እንደሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት ሁሉ ለመመለስ የሚያስቸግሩ ይኾናሉ። ሕግ አክብረው የሚሠሩትን ወደ ሕገወጥነት የሚመልስ በመኾኑ ሊታሰብበት ይገባል። ሕገ ወጥ ሥራን አለመከላከል ከሕጋዊው የሚገኘውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና የመንግሥት ገቢንም የሚያሳጣም ነው ።
በከፍተኛ ጩኸት ማስተዋወቅ ምንም እንኳ ሠርቶ ለማደር የሚደረግ ጥረት ቢኾንም እረፍት የሚነሳ፣ ሰላማዊ ኑሮን የሚረብሽ፣ ለአደጋም የሚያጋልጥ ነው። ሕጋዊ ኾነው እና በታወቀ አድራሻ የሚሠሩትንም መብትና ጥቅም ይጎዳል። ሕገ ወጥነትን የሚያለማምድም ስለኾነ አስቀድሞ ሊስተካከል ይገባዋል ነው ያሉት የሕግ ባለሙያው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!