
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተከዜ ተፋስስ በተለይም በዋግኸምራ፣ ሰሜን ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ ይከሰታል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ዘንድሮ በተከሰተ የድርቅ አደጋ በርካታ ወገኖች ለችግር መዳረጋቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አያሌ እንስሳት ደግሞ በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን ዘግበናል፡፡
ከአሁን ቀደም ድርቅን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሩያ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጥናት መምህር ጋሻው ቢምረው (ዶ.ር) የአየር ንብረት ለውጥ፣ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው የሙቀት መቀያየር፣ የደኖች መራቆት፣ የሕዝብ ብዛት፣ ውኃን በአግባቡ ያለመያዝ ችግር እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ድርቅ እንዲከሰት ያደርጋሉ ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ መልካዓ-ምድራዊ አቀማመጥ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲመጣ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡ የፓስፊክ ውቅያኖስ ሙቀት መቀያየር ድርቅን ይዞ ይመጣል። ቀደም ሲል በአሥር ዓመታት ይመጣ የነበረው ድርቅ በአምስት ዓመታት እና በሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲከሰት እያደረገ መኾኑንም ያነሳሉ፡፡
የአካባቢ መራቆት በተፈጠረ ቁጥር ውኃን የመያዝ አቅሙ ይቀንሳል፤ የከርሰ ምድር ውኃም ወደታች ይወርዳል፤ ይሄም ድርቅን ይዞ ይመጣል ነው ያሉት፡፡ ሕዝብ በበዛ ቁጥር መሬቶችን በመቆራረስ መጠቀም ይመጣል፤ የመሬት አያያዙም አነስተኛ ይኾናል፤ ይሄም ድርቅን ያመጣል ይላሉ መምህሩ፡፡ ውኃ በስፋት አለን የሚሉት መምህሩ የውኃ አያያዛችን ግን ዝቅተኛ ነው፣ ውኃን በአግባቡ አንጠቀምበትም ነው ያሉት፡፡
ውኃን ማጠራቀም ከተቻለ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት መጠቀም ይቻላል፤ ድርቅንም መቋቋም ያስቸላል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአማካኝ ከፍተኛ የኾነ የዝናብ መጠን አለ፤ ነገር ግን በአግባቡ መጠቀም አንችልም ይላሉ፡፡ በፖለቲካዊ ችግሮች ምክንያት አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ ይኾናሉ። የግብዓት አቅርቦትም ያጣሉ ይሄም ለድርቅ ያጋልጣል፤ ድርቅን ለመቋቋም እንዳይቻል ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡
በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚከሰተውን ተደጋጋሚ ድርቅ የውኃ አያያዝን በማሻሻል መቋቋም ይቻላል ነው የሚሉት፡፡ የውኃ አያያዝ ላይ ካልተሠራ ግን ተከዜ በራሱ አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ፡፡ ድሮ ከዓመት እስከ ዓመት ይፈሱ የነበሩ ወንዞች አሁን ጊዜያዊ እየኾኑ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ድርቅን ለመቀነስ እና ለመቋቋም ከግለሰቦች ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ ለድርቅ ተጋላጭ ላለመኾን አቅም መገንባት እንደሚቻልም ተናግረዋል። የሚጠበቅብንን መሥራት ባለመቻላችን ከድርቅ ጋር እየኖርን ነው ብለዋል፡፡ በድርቅ እንደመጠቃት አዋራጅ ነገር የለም ይላሉ፡፡ ውኃ ላይ ብቻ በመሥራት የድርቅ አደጋን መቀልበስ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡
👉 በተከዜ ተፋሰስ የሚገኙ አሥተዳደሮችስ ምን እየሠሩ ይኾን?
የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲሱ ወልዴ የተፈጥሮ ሀብት በመመናመኑ ምክንያት በዋግኸምራ ብሔሰረብ አሥተዳደር ተደጋጋሚ ድርቅ ይከሰታል ብለዋል። ድርቅን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ለበርካታ ዓመታት እንደተሠሩም ይናገራሉ፡፡ በተለይም ለተፈጥሮ ሀብት ትኩረት በመስጠት ሲሠራ ኖሯል፤ ነገር ግን የተሠራው ሥራ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ባለመቻሉ እስካሁን ድረስ ድርቅ እየተከሰተ ነው ይላሉ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ለዋግኸምራ ሲፈለግ የሚተው ሲፈለግ የሚሠራ ሳይኾን የሕልውና ጉዳይ ነው የሚሉት ኃላፊው በአረንጓዴ አሻራ እና አረንጓዴ አሻራ ከመጀመሩ አስቀድሞ በዋግ ከፍተኛ ቦታዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ሲተከሉ መቆየታቸውንም አንስተዋል፡፡ አካባቢን መሠረት ያደረጉ ችግኞችን በመትከል በኩል ግን ጉድለቶች ነበሩብን ነው የሚሉት፡፡ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን መንከባከብ ወሳኙ ነው ያሉት ኃላፊው የችግኝ ዝግጅት እና ከተተከሉ በኋላ ያሉ እንክብካቤ ላይ ትኩረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ድርቅን ለመከላከል ችግኝ ከመትከል ባለፈ የውኃ እቀባ ሥራዎችም በትኩረት እየተሠራባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ድርቅን ለመከላከል ወሳኙ ጉዳይ ነው የሚሉት ኃላፊው በዋግኸምራ ሰፋፊ መሬቶችን ሊያለሙ የሚችሉ ወራጅ ወንዞች አሉ፣ መስኖን መጠቀም ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው ወረዳዎች በጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድ የመስኖ ሥራዎችን መሥራታቸውንም አንስተዋል፡፡ ታላላቅ የመስኖ ፕሮጄክቶችን መገንባት በአካባቢው የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ይፈታልም ይላሉ፡፡ በዚህ ዓመት 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኞች በችግኝ ጣቢያ ተዘጋጅተው ለተከላ ለማቅረብ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ 60 ሺህ ችግኞች ደግሞ የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው ብለዋል፡፡ ማኅብረሰቡ የልቅ ግጦሽን ማስቀረት፣ መከለል እና መጠበቅ ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ጌታቸው አዳነ ዞኑ በተደጋጋሚ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያጠቃው እና ተደጋጋሚ የድርቅ ችግር የሚከሰትበት ነው ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመቋቋም አካባቢውን በደን ልማት መቀየር አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች በረጅም ጊዜ ሥራ የሚመለሱ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
ለመኖ፣ ለፍራፍሬ እና ለደን ልማት አገልግሎት ሊወሉ የሚችሉ ችግኞች ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በሚተከለው ልክ በማይጸድቅባቸው አካባቢዎች የችግኝ ዝርያዎችን ለመምረጥ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ለማስጠናት በሂደት ላይ ነን ብለዋል፡፡ 61 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ላይ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ 33 ሚሊዮን የሚኾኑ ችግኞች ለተከላ ደርሰዋል ነው ያሉት፡፡ 159 ሺህ የሚኾኑት ደግሞ የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው ብለዋል፡፡
10 ሺህ 748 ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዷል ነው ያሉት፡፡ 7 ሺህ 500 የሚኾነው ሄክታር ደግሞ ተለይቷል ብለዋል፡፡ ተጨማሪ የመትከያ ቦታዎችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ዞን እየተሠራው ያለው ሥራ ብቻ የአየር ንብረት ተጽዕኖውን ሊቋቋመው አይችልም ነው ያሉት፡፡ ችግሩን በሂደት ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሰፊ ትኩረት የተሰጣቸው ደግሞ ድርቅ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸው ናቸው፡፡
ከግብርና መምሪያ በተጨማሪ በዘርፉ የሚሠሩ ፕሮጄክቶችን ማስገባታቸውንም አንስተዋል፡፡ የእርጥበት እቀባ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡ ችግኞችን ከንክኪ ነጻ ማድረግም ሌላው ሥራ ነው ተብሏል፡፡ አርሶ አደሮች የችግሩ መፍትሔዎችም ተጋላጮችም ናቸው ያሉት ኃላፊው የተፈጥሮ ደኖችን ከማቃጠል ወጥተው መንከባከብ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ንጉሤ ማለደ ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ችግኝ መትከል እና ከሌሎች መጠበቅ ድርቅን ለመከላከል ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች በርካታ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
በተለይም ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የአፈር እና ውኃ እቀባ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ሥራ በትኩረት እንደሚሠራባቸው ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም አካባቢውን ለማቅናት ቀናኢ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተሠራው ልክ ግን ውጤት አልተገኘም ነው ያሉት፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች በልዩ ትኩረት ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ጥቅም ያላቸው ችግኞች ቅድሚያ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል፡፡
140 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል፡፡ ድርቅ በሚከስተባቸው አካባቢዎች ደግሞ የመኖ እና የፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት ይደረግባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ድርቅን ሊቋቋሙ የሚችሉ የግብርና ምርምር ውጤቶችን ለመተግበር ከምርምር ተቋማት እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት ውጤት የሰጡ የምርምር ውጤቶች መገኘታቸውንም አንስተዋል፡፡
ፕሮጄክቶች እና የምርምር ተቋማት ምርጥ ዘር ላይ እንዲያግዟቸው ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ የተሠሩ ተፋሰሶችን መጠበቅ፣ ተራራዎች የውኃ ጋን እንዲኾኑ የሚሠሩ ሥራዎችን እና ችግኞችን በመንከባከብ አካባቢው እንደሌሎች አካባቢዎች እንዲኾን ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ድርቅ እንዳይከሰት፣ እንስሳትም እና ሰዎች እንዳይጎዱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!