የአረንጓዴ አሻራ ቅድመ ዝግጅት!

45

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ለ2016/17 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ የተፈጥሮ ሃብትን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ መኾኑም ተገልጿል።

በአማራ ክልልም በበጀት ዓመቱ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች በግለሰብ፣ በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የወገራ ወረዳ አርባ አራት ችግኝ ጣብያ አንዱ ነው። በጣቢያው የሠራተኞች ተቆጣጣሪ አዳነ ደምሌ እንደነገረን በአካባቢው ለአምስት ዓመት ያህል የተለያዩ ችግኞችን በማፍላት የተራቆቱ የወል እና የይዞታ መሬቶች ላይ ችግኝ የመትከል ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በዚህ ዓመትም እስከ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ እየተዘጋጀ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ እንደዲከረንስ፣ ወይራ፣ ጌሾ፣ ጥድ እና የከብት መኖ ችግኞች ይገኙበታል። ይህም ከተለያዩ አካባቢዎች ለችግኝ ይወጣ የነበረውን ወጭ ማስቀረት ተችሏል። እንደ ጌሾ የመሳሰሉ ችግኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡን በማቅረብ ምጣኔ ሃብታዊ አቅማቸውን ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል። በችግኝ ጣብያው 13 ሠራተኞች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዚገም ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ደን ባለሙያ ተመስገን ገዛኸኝ እንዳሉት ደግሞ በዚህ ዓመት 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ የደን እና የመኖ ችግኝ ተዘጋጅቷል። ከዚህ ውስጥ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው የደን ችግኝ ነው። እንደ ዋንዛ፣ ብሳና፣ ወይራ፣ ሽመል፣ ጌሾ፣ ቁንዶ በርበሬ የመሳሰሉ ሀገር በቀል እና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።

ተከላው 18 ቀበሌዎች ላይ ይካሄዳል። በአንድ ቀን ጀምበር 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ተዘጋጅቷል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን እና የምጣኔ ሃብት አቅምን የማሳደግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት ለ2016 ዓ.ም ክረምት የሚተከሉ ከ987 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ219 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው ችግኝ የጽድቀት ምጣኔን ለመጨመር በፕላስቲክ የተዘጋጀ ነው፤ ከ150 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው ደግሞ ሀገር በቀል ችግኝ መኾኑን አንስተዋል። በክልሉ በ63 ሺህ 393 የግለሰብ፣ ከ1 ሺህ 400 በላይ የማኅበራት፣ በ104 መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች፣ በ773 የመንግሥት ችግኝ ጣብያዎች እና በ1 ሺህ 457 የተቋማት የችግኝ ጣብያዎች የማልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ 130 ሺህ 773 የሚኾኑ ደረጃቸውን ባልጠበቁ ቦታዎች አርሶ አደሮች እያለሙ ይገኛል ነው ያሉት።

በግለሰብ የችግኝ ጣቢያዎች እንደ ባሕር ዛፍ፣ ዲከረንስ እና ጌሾ የመሳሰሉ ችግኞች በብዛት የተዘጋጁ ሲኾን በመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች ደግሞ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው እና ሀገር በቀል ዝርያዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል። አሁን ላይ የደረሰውን ችግኝ ውኃ ማጠጣትን በመቀነስ፣ በፀሃይ በማስመታት፣ ሥሩን በመግረዝ ችግር የማለማመድ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የችግኝ የተከላ ቦታ ለማዘጋጀትም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት በቂ በጀት ባለመመደቡ በፕላስቲክ የማፍላት ምጣኔው ከባለፈው ዓመት መቀነሱን ገልጸዋል። በቂ የሀገር በቀል ችግኝን ለማዘጋጀትም አለመቻሉን ነው ያነሱት። ባለሙያው የተፈላውን ችግኝ ቆጥሮ መረጃ የመያዝ፣ የደረሰውን ችግኝ ችግር የማለማመድ እና ችግኙ የሚተከልበትን ቦታ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እየተመራሁ መጥቼ እያየሁ ተመልሻለሁ” ታካሚ
Next articleበተከዜ ተፋሰስ ድርቅን ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው?