
ሰቆጣ: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መመሪያ ከ760 በላይ ለኾኑ ሰዎች ነጻ የዐይን ቀዶ ህክምና በማድረጉ የዐይናቸው ብርሃን ተመልሶላቸዋል፡፡ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ሊከሰት እና የዐይን ብርሃንን ሊያሣጣ የሚችል በሽታ እንደኾነ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህ በሽታም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብቻ ከ1 ሺህ 500 በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች በበሽታው መጠቃታቸውን ከጤና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ከቤተ አብርሃም እና ሂማልያ ከተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል በነጻ የዐይን ሞራ ቀዶ ህክምና ተደርጓል። መሪጌታ ዮናስ ቀለሙ ባለፋት ስምንት ዓመታት የዓይን ብርሃናቸውን በማጣት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደነበር ይገልጻሉ።
ከሚወዱት አገልግሎት ከመራቃቸውም ባሻገር ቤተሠባቸውን የመምራት አቅም አጥተው እንደነበርም ያስታውሳሉ።አሁን ግን ዳግም ተወልጃለሁ ያሉት መሪጌታ ዮናስ ቀዶ ጥገና ያደረጉላቸውን አካላትም አመስግነዋል። ወይዘሮ መብራቴ መኮንን ከሦስት ዓመት በፊት ባጋጠማቸው የዐይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ከቤቱ ውለው የነበረ ቢኾንም በተደረገላቸው ቀዶ ጥገና ብርሃናቸውን ማግኘታቸውን ይገልጻሉ። “እየተመራሁ መጥቼ እያየሁ ተመልሻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
በተፈራ ኃይሉ ሆስፒታል የዐይን ህክምና ባለሙያው ልጃለም ወልዴ በበኩላቸው በቅርበት የዐይን ህክምና ባለመኖሩ ችግሩ እንደተባባሰ ገልጸዋል። የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም በባለሙያ የተነገሩትን መልዕክት እንዲተገብሩ መክረዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ አሰፋ ነጋሽ ከቤተ አብርሃም እና ሂማልያ ድርጅት ጋር በመተባበር በተደረገው የዐይን ሞራ ቀዶ ህክምና የ769 ሰዎች የዐይን ብርሃናቸው እንደተመለሰ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በቅርበት የዐይን ስፔሻሊስቶች በሆስፒታሉ እንዲመደቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ ኀላፊው ድጋሚ የዐይን ሞራ ቀዶ ህክምናውን እንዲሠሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተነጋገሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ኀላፊው ግብረሰናይ ድርጅቶች ስላደረጉት ድጋፍ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!