የግብርናው ዘርፍ ባለፉት 10 ወራት የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እንደነበር የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

27

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር የ10 ወራት አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው። በግምገማው ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ባለፉት ወራት በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ውጤቶች መታየታቸውን ተናግረዋል። መስኖ ከአምናው የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጸዋል።

ዶክተር ግርማ አፈጻጸሞችን በቁጥር ሲያስቀምጡ:-
👉 ወቅታዊ የመስኖ ስንዴን 3 ሚሊዮን ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ማሳካት ተችሏል።
👉120 ሚሊዮን ኩንታል የመስኖ ስንዴ ለመሠብሠብ ታቅዶ ከ90 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መሠብሠብ ተችሏል።
👉 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበልግ እርሻ ለማልማት ታቅዶ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተሸፍኗል።
👉 ሰው ሠራሽ ማዳቀል ላይ በ2016 ዓ.ም ከታቀደው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ውስጥ በዘጠኝ ወር 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
👉 የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለአፍሪካ ቀርቧል።
👉 በዓመት ከ92 ሺህ ሄክታር በላይ የነበረውን የደን ጭፍጨፋ ወደ 32 ሺህ ሄክታር መቀነስ ተችሏል።
👉 አሁን ላይ ከ6 ሺህ በላይ የለሙ ተፋሰሶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ለቀጣዩ የችግኝ ተከላ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
👉 ተከላ ሊደረግበት ከታሰበው መሬት አኳያ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መዘጋጀቱም ተገልጿል።
👉 35 በመቶ የደን ችግኞችም በለሙ ተፋሰሶች የሚተከሉ ናቸው ነው ያሉት።
👉 650 ሺህ ሄክታር መሬት ካርታ ወጥቶላቸው ችግኞች ይተከላሉ ያሉት ሚኒስትሩ እስካሁን 600 ሺህ ሄክታሩ ካርታ ወጥቶ መለየቱን ገልጸዋል።
👉 ሚኒስትሩ ከአምናው ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው የግብዓት አቅርቦት አለ ብለዋል።
👉ዘንድሮ 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አስቀድሞ የተገዛ ሲኾን 12 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል እስከዛሬ ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።
👉 እስካሁን 50 በመቶ ማዳበሪያ ማሠራጨት መቻሉን ሚኒስትሩ አንስተው ስርጭቱ የተሻለ እንዲኾን ክልሎች የዲጂታል ሥርጭት መንገድን ጨምሮ በከፍተኛ ደረጃ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የግብርና ልማት ፖሊሲ አዋጅ ተሻሽሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ትልቅ እርምጃ እንደኾነም ነው ያስረዱት። የግብዓት አቅርቦት እና ሥርጭት፣ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ስለመኾናቸው አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾኑን ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ገለጹ፡፡
Next article“እየተመራሁ መጥቼ እያየሁ ተመልሻለሁ” ታካሚ