
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾኑን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ304ኛ ኮር ዋና አዛዥና የአዊና የሰሜን ጎጃም ዞኖች ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪዎች በወቅታዊ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ጋር መክረዋል።
ነዋሪዎችን ያወያዩት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ304ኛ ኮር ዋና አዛዥ የአዊና የሰሜን ጎጃም ዞኖች ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ጽንፈኛ ኀይሎች በአመጽ እና በብጥብጥ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያደረጉት ጥረት ዘመኑን የማይመጥን እና ውጤት የማያመጣ መኾኑን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ አስገንዝበዋል። ኅብረተሰቡ ግጭትን የገቢ ምንጭ ያደረጉ አካላትን በመታገል ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎችም ለአካባቢያቸው ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተለያዩ አካባቢዎች በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በቀጣናው የተሰማራው የሀገር መከላከያ እና የክልሉ የፀጥታ ኀይል ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ወደ ቀድሞ ሰላሙ ለመመለስ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
መሪዎች ከፀጥታ አካላት እና ከሕዝቡ ጋር ባደረጓቸው ተደጋጋሚ መድረኮች ኅብረተሰቡ የሰላም ባለቤት እየኾነ መምጣቱን ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል። በግጭቱ ምክንያት ዜጎች በተፈናቀሉባቸው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አካባቢዎች ጠንካራ የፀጥታ ኀይል በማደራጀት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!