
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክር ቤቶች ጠቃሚ እሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ እና የኅብረተሰቡን አብሮነት የሚያጠናክሩ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሠሩ መኾኑን የተለያዩ ክልሎች አፈ ጉባኤዎች ገልጸዋል። በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማነት ክትትል እና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የአማራ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች አፈ ጉባዔዎች በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የሕዝብን ውክልና ይዘው እንደመሥራታቸው ለኅብረተሰቡ አብሮነት እና ዘላቂ ሰላም መፍትሔ በሚኾኑ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሠራሉ ብለዋል። በተለይም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት እና የእርስ በእርስ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ የጋራ ጉዳዮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውም ነው ያነሱት።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቡቶ አኒቶ ኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት ያላት እንደመኾኗ ልዩነቶችን ተቀብሎ በሰላም እና በትብብር ለመኖር ውይይት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የጋራ ጉዳዮችን የሚያጎሉ እሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በጋራ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ልዩነቶችን መፍታት የጋራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ በመኾኑ ምክር ቤቶች የተጣለባቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ይሠራሉ ብለዋል። ምክር ቤቶቹ የሚከታተሏቸው አስፈጻሚ አካላት የጋራ እሴት ግንባታ ላይ አጽንኦት ሰጥተው እንዲሠሩ አቅጣጫ አስቀምጠው እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ “በረጅም ጊዜያት የተገነቡ ጠቃሚ ሀገራዊ እሴቶችን በትምህርት ካሪኩለም ቀርጾ ማስተማር የጋራ ትርክትን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው” ብለዋል። ግብረ ገብነት፣ ታታሪነት፣ አርበኝነትን ጨምሮ ያሉትን የጋራ እሴቶች ለትውልዱ እንዲተላለፉ ማድረግ አብሮነትን ለማስቀጠል ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ መሰለ ከበደ ሀገራዊ እሴቶችን የጋራ ለማድረግ እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ምክር ቤቶች ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ ብለዋል። በየክልሉ ያሉ ጠቃሚ እሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ምክር ቤቶች ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤዎቹ ምክር ቤቶች የኅብረተሰቡን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እንደሚሠሩም ነው ያብራሩት። ኢዜአ እንደዘገበው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!