
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመኸር እርሻ የግብርና ግብዓት የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ግብርና ቢሮ ገልጿል። ቢሮው በ2016/17 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሠራ ይገኛል። በምርት ዘመኑ የሰብል ልማት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፍላጎትን ማሟላት፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና ወደ ውጭ ለመላክ ጭምር ትኩረት ተደርጓል።
የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት ምን እየተሠራ እንደሚገኝ የግብርና ባለሙያዎችን አነጋግረናል። ካነጋገርናቸው ባለሙያዎች ውስጥ በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የቀበሌ ግብርና ባለሙያዋ ጎጃም ታያቸው አንዷናቸው። ባለሙያዋ እንዳሉት አርሶ አደሮች በኩል በትራክተር ጭምር ማሳን የማለስለስ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጭምር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የቀረበውን ግብዓት እና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ለማቅረብ ድልድል መሠራቱንም ነው የገለጹት። ከደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ የቀበሌ ግብርና ባለሙያ ሙሉቀን ሲሳይ እንዳሉት ቀድመው ዘር ለሚዘሩ አካባቢዎች ማዳበሪያ እየተሠራጨ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ለማዋል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንደገለጹት በተያዘው የምርት ዘመን የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን እና ግብዓትን በሙሉ ፓኬጅ ለመጠቀም ትኩረት ተደርጓል። በዚህ ወቅት የግብዓት አቅርቦት እና የማሣ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። እስከ አሁንም ግዥ ከተፈጸመው ከ8 ነጥብ 05 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ኾኗል። ከዚህም በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመጠቀም የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአፈር ለምነት እና ሰብል ጥበቃ ላይ ያተኮረ በክልሉ ለሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሠጥቷል ብለዋል። አሁን ላይ በደጋማ እና ወይና ደጋ አካባቢ እንደ በቆሎ፣ ድንች እና ማሽላ የመሳሰሉ ዘር መጀመሩን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ደግሞ እስከ ሦስተኛ እርሻ ማሣን የማለስለስ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በምርት ዘመኑ በሄክታር 32 ነጥብ 4 ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!