“የኮሙኒኬሽን እና የሬዲዮ ሲግናልን በአግባቡ ማሥተዳደር የዲጅታል ሥነምህዳሩን ከማስተካከል ባለፈ ሀብትን በአግባቡ እና በፍትሐዊነት የመጠቀም ጉዳይ ነው” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)

36

አዲስ አበባ: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የኮሙኒኬሽን ሲግናል ጉባኤ መካሔድ ጀምሯል፡፡ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ቴክኒካል ኮንፈረንስ ከግንቦት 12/2016 ዓ.ም እስከ ግንቦት 14/2016 ዓ.ም የሚካሔድ ነው።

ኮንፈረንሱ በተለይ ሀገራት የሳተላይት፣ የባሕር እና የየብስ የኮሙኒኬሽን ሲግናል እንዲሁም የሬዲዮ ሲግናልን በአግባቡ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ነው። 53 የአፍሪካ ሀገራት በአካል እና በበይነመረብ እየተሳተፉበት የሚገኘው የአዲስ አበባው ኮንፈረንስ የሳተላይት ምህዋር አጠቃቀም እና የኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማቶች ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይም እየመከረ ነው የሚገኘው።

ኮንፈረንሱን የከፈቱት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የኮሙኒኬሽን እና የሬዲዮ ሲግናልን በአግባቡ ማሥተዳደር የዲጅታል ሥነምህዳሩን ከማስተካከል ባለፈ ሀብትን በአግባቡ እና በፍትሐዊነት የመጠቀም ጉዳይ ነው ብለዋል። ጉባኤው ሀገራት የኮሙኒኬሽን ሲግናልን መጠቀም የሚችሉበት መመሪያ ዙሪያም ይመክራል።

ይህ ኮንፈረንስ በተለይ ሀገራት የወታደራዊ እና የደኅንነት መገናኛቸውን በተመለከተ፣ የሜትሪዎሎጂ፣ የቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችን፣ የስለላ እና የባሕር ላይ መገናኛዎችን፣ የአስትሮኖሚ እና የመሬት ጥናቶችን የተመለከቱ መሰረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች ላይ እንደሚያተኩር ነው የተገለጸው።

ዘጋቢ ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) በፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ።
Next articleግብዓት የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ግብርና ቢሮ ገለጸ።