ኢኮኖሚውን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን የፕላን እና ልማት ሚንስቴር አስታወቀ።

38

አዲስ አበባ: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘጠኝ ወራት ሀገራዊ የልማት ሥራዎች አፈጻጸም ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሠጡት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፋፁም አሰፋ (ዶ.ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር በተለይም በማይክሮ ኢኮኖሚ፣ በመሰረተ ልማት እና በፕሮጀክት አፈጻጸም የተሻለ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

በሕዝባዊ ተሳትፎ፣ በሪፎርም ሥራ አፈጻጸም በአጠቃላይ ልማት እና የሪፎርም ሥራዎች ክትትል እና ድጋፍ በኩል የተሠሩ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና ውስጥ ብትኾንም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፍ በተከናወኑ ሥራዎች እንደሀገር ለማሳካት የታቀደውን 7 ነጥብ 9 የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት የተሄደበት ርቀት አበረታች መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሠሩ ሥራዎች ይህንን የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት የሚያስችሉ መኾናቸውን ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደሀገር የታቀደውን 7 ነጥብ 9 የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት በግብርናው ዘርፍ ጥቅል ሀገራዊ ምርትን በማሳደግ በሰብል ምርት በተለይም በስንዴ ምርት ከአምናው ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እድገት ተመዝግቧል። በእንስሳት ሃብት በዶሮ፣ በወተት እና ሥጋ፣ ዓሣ እና ማር ላይ ትኩረት ተደርጎ በተሠራው የሌማት ቱሩፋት ሥራም አመርቂ ውጤት መገኘቱ ተመላክቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለተገኘው አመርቂ ውጤት የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም ማደግ የግብዓት አቅርቦት መሻሻል ለተገኘው እድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ተብሏል። በአገልግሎት ዘርፉም ቢኾን ከፍተኛ የገቢና የወጭ ንግድ እድገት መኖሩ የጅምላ እና ችርቻሮ ንግዱ መሻሻል ማሳየቱ በተለይ በትራንስፖርት በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምና ከነበረው በተሻለ በተያዘው በጀት ዓመት ከ25 በመቶ በላይ ያደገ አፈጻጸም ማሳየቱ በቱሪዝም ዘርፉም ቢኾን ከአምናው በተሻለ መልኩ ዘንድሮ ከ100 ሺህ በላይ ጎብኝዎች እንደተሳተፉ ተመላክቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዲጂታል ኢኮኖሚ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፉ የታዩ እድገቶች እንደ ሀገር የተያዘውን 7 ነጥብ 9 ሀገራዊ የእድገት ትንበያ ያሳካሉ ብለዋል ሚኒስትሯ በመግለጫቸው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሎችን ገቢ ከማሳደግ፣ የፋይናንስ ዘርፍን ከማሻሻል፣ የሸቀጣ ሸቀጦችን የውጭ ንግድ ከማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬን ግኝትን ከማሳደግ በተለይም የሥራ እድል ፈጠራን ከማሳደግ የዋጋ ንረትን ከማስተካከል አንጻር የተሠሩ ሥራዎችም አበረታች መኾናቸው በመግለጫው ተነስቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስኬቶች ብቻ ሳይኾን ጉድለቶችም እንደነበሩ ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡ በቀጣይ የተሻለ ሀገራዊ እድገት እንዲመዘገብ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት በተለይ የግሉ ዘርፍ በስፋት ወደ ሥራ እንዲሠማራ በማድረግ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በመስጠት የሀገራችንን እድገት የበለጠ ለማስቀጠል እና ኢኮኖሚውን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እና ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ሰለሞን አሰፌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next articleየአፍሪካ ኅብረት በኢራን መሪዎች ድንገተኛ ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገለጸ።