
አዲስ አበባ፡ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በወጣቶች ዙሪያ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፎረም ምስረታ መድረክ ተካሂዷል ። በመድረኩ ከወጣቶች ጋር በተያያዘ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ወጣቶች ለሀገር የጀርባ አጥንት ናቸው ያሉት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ወጣቶች ህልም አላሚዎች፣ አዳዲስ ነገር ፈጣሪዎች፣ የዛሬ እና የነገ መሪዎች በመኾናቸው የወጣቶችን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በወጣቶች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የበለጸገች፣ ሁሉን አቀፍ እና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ መኾኑንም ጠቁመዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡ የተዘጋጀው ፎረም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማጎልበት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የጋራ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በወጣቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች በቅደም ተከተል ለመፈጸም፣ ተቋማቱ በስቴራቴጂዎች እና በፕሮግራሞች በተገቢው መልኩ አካተው እንዲሠሩ ማድረግ የዚህ ጥምረት ዋነኛ ዓላማ መኾኑን ጠቁመዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡ ወይዘሮ ሙና የወጣቶችን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ለመፍታት በመንግሥት እና በአጋር አካላት መካከል ትብብር እና ቅንጅትን በማጠናከር በጋራ ለመሥራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወጣቶች ላይ ከሚሠሩ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ይሠራልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!