
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ግጭት በሰው ልጆች የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አንዱ ገጽታ ነው። ግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መቆጣጠር ደግሞ አንዱ ጥበብ ነው። የሚፈጠሩ ግጭቶችን ቀድሞ ለመፍታት ከሚያገለግሉ መንገዶች ውስጥ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው።
ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማቱ ለመቻቻል፣ ለእኩልነት፣ ለመልካም አሥተዳደር መስፈን እና ለፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በመፍታት ሰላም እንዲፈጠር ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ያላቸው፣ በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመኾናቸው በተገልጋዮች ዘንድ የሚታመኑ ናቸው፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ በመለየት እና ግጭቶችን የመከላከል ሚናቸው የጎላ ነበር። በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልኾነባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላምን በማስፈን እና ፍትሕን በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።
በአካባቢው የሚሰየሙ ጉምቱ ሽማግሌዎች መረጃዎችን መሠረት አድርገው ሰላምን ሊያመጣ በሚችል ሁኔታ የእርቅ ሥነ ሥርዓቱን ይፈጽማሉ። ሽማግሌዎቹ የእድሜ ባለፀጋ በመኾናቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ከሕግ ይልቅ የሕሊና እና ማኅበራዊ ኀላፊነትን በመጠቀም ሁለቱን አካላት ወደ ሰላም መንገድ ያመጣሉ።
የችግር አፈታቱም በቤት ውስጥ በባል እና ሚስት መካከል ከሚፈጠር ችግር ጀምሮ በቀዬ ውስጥ እስከሚፈጠር የመሬት ሙግት፣ በደም የተቃቡትን እስከማስታረቅ፣ ሸፍቶ ጫካ የገባን መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር እስከመቀላቀል፣ አልፎ ተርፎም በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረጉ የእርቅ ሥነ ሥርዓቶችን ያጠቃልላል።
ሀገር በቀል ተቋማቱ በሕቡዕ ተፈጽመው በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮችን ጭምር በመሃላ፣ በእርግማን፣ በምርቃን፣ በካሣ እና በመሳሰሉ መንገዶች አጥፊውን በመቅጣት እና ተበዳዩን በማስካስ ስለሚያከናውኑ እርቁ እውነት የኾነ፣ በድጋሜ ለቂም በቀል የማያነሳሳ ነው። እርቁንም የጸና ስለሚያደርገው ከመደበኛ የፍትሕ ሥርዓቱ በተሻለ መንገድ ችግር ፈቺ ተደርገው ይወሰዳሉ፤ ይህም በማኅበረሰቡ ይበልጥ ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
ዘመናዊ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ባለው አካል ላይ ውሳኔ ከመስጠት ውጭ በበዳይ እና በተበዳይ መካከል ስለተፈጠረው የእርስ በርስ የመፈላለግ ስሜት ምንም ዓይነት ተግባር አይፈጽምም። ለዚህ ነው በመደበኛ ፍርድ ቤት ሂደት ገዳይ ከተፈረደበት በኋላ በሽማግሌ አማካይነት የገዳይ እና የሟች ቤተሰቦች ለበቀል እንዳይፈላለጉ የእርቅ ሥነ ሥርዓት እንዲከናወን የሚያደርጉት። በመኾኑም በሽምግልና ሥርዓት ግጭቶች በእርቅ ሲፈቱ ዋና ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ላይ ነው።
የሽምግልና እሴት ለማኅበረሰቡ ያለው ጠቀሜታ ታውቆ የበለጠ ልንጠቀምበት የሚገባ ማኅበራዊ የሰላም ቋንቋ እንደኾነ ኢንጅነር አድማሱ ገበየሁ (ዶ.ር) “መግባባት” በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ አስቀምጠውታል። ኢንጅነር አድማሱ በዚሁ መጽሐፋቸው ባሕላዊው የሽምግልና ሥርዓት ተመራጭ እንዲሆን ያስቻሉ ጥንካሬዎችን ያመላክታሉ። ከእነዚህ ውስጥም:-
👉 በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ በቀና፣ በተስተካከለ እና በእውነተኛ መንገድ መከናወኑ፣
👉 ባሕላዊው የሽምግልና ተቋም በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኝ እና ከራሱ ከማኅበረሰቡ የተዋቀረ መኾኑ፣
👉 በቅርብ የሚገኝ ስለኾነ አንድ ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት ወዲያው ወደ ግጭቱ አካባቢ መድረስ መቻሉ፣
👉 ግጭቱ እንዲቀዘቅዝ እና በዘላቂነት በእርቅ እንዲፈታ ለአፈጻጸም የሚመቹ ባሕላዊ ዘዴዎችን መጠቀሙ፣
👉 ግጭቶች ተባብሰው የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ አካል አንዳይጎድል እና ንብረት እንዳይወድም ከጅምሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረጉ፣
👉 በመደበኛው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ሊገለጹ እና ሊታወቁ የማይችሉ የተሸፈኑ (የተደበቁ) ነገሮች በሽምግልና ሥርዓት ላይ በሚፈጠረው ባሕላዊ እና የእውነተኛነት ድባብ ግልጽ እንዲወጡ ማስቻሉ እና
👉 የባሕላዊ እርቅ ሂደት የተጋጩት ወገኖች በጥፋታቸው ተጸጽተው እና ቂማቸውን ፍቀው ወደፊት ተባብረው እና ተፋቅረው በአንድነት እንዲኖሩ ማስቻሉ ዋና ዋና የባሕላዊ ሽምግልና ጥንካሬዎች ናቸው።
ለመኾኑ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ወደ ቀደመ ተግባራቸው ለመመለስ ምን እየተሠራ ይኾን? የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ባለሙያ ደርበው ጥላሁን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማት በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም ባለፉት ጊዜያት ተገቢው ሕጋዊ እውቅና ባለመሰጠቱ እንደ አውጫጭኝ እና አፈርሳታ የመሳሰሉ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች መዳከማቸውን አንስተዋል።
የአማራ ክልል የሽምግልና ማኅበር ተቋማቱን ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ቢገኝም ካለው የግጭት ስፋት አኳያ አሁንም በተፈለገው መንገድ እየተከናወነ አለመኾኑን አንስተዋል፡፡ ተቋማቱን ወደ ቀደመ ማንነታቸው ለመመለስ ከክልል እስከ ቀበሌ ተዋጽኦውን በጠበቀ እና ችግር ፈች በኾነ መንገድ የክልሉን የሽግልና መማክርት ጉባኤ ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮም ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ለሰላም ግንባታ ካላቸው ሚና አኳያ ስያሜያቸውን፣ አስፈላጊነታቸውን፣ አሁን ያሉበትን ደረጃ እና መሰረታዊ ችግሮቻቸውን ከቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት የመለየት እና የመመዝገብ ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በ2015 ዓ.ም ለሀገር ሽማግሌዎች ሥልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል።
ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንደ አንድ ተቋም ተደራጅተው ማንኛውንም ተግባር በራሳቸው በመከወን የዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓቱ አጋዥ እንዲኾኑ መንግሥት በተለየ መንገድ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል። በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ግጭትን በባሕላዊ መንገድ የመፍታት ባሕሉ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ እሴቱን የማሻገር ችግር በማጋጠሙ በሀገሪቱ ያልተለመደ ባሕል እየተንጸባረቀ፣ አብሮ የመኖር እና የመቻቻል ባሕል እየተሸረሸረ እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል። አሁን ላይ ይህንን እሴት በማጠናከር የችግር መፍቻ ለማድረግ ቢሮው እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። በክልሉ እንደ ሽምግልና የመሳሰሉ በርካታ የግጭት መፍቻ መንገዶች መኖራቸውን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በክልል ደረጃ የተለያዩ አካላት የተካተቱበት የሽምግልና መማክርት ጉባኤን ለማጠናከር የሚያግዙ የሰነድ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል። በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር እና በበጀት እጥረት ምክንያት በተፈለገው መጠን ወደ ሥራ መግባት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!