የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተጠቆመ፡፡

19

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ትኩረት መደረግ እንዳለበት የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ከ10 ወረዳዎች የተውጣጡ አመራርና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአሲዳማ አፈር የንቅናቄ መድረክ በደብረብርሀን ከተማ ተካሂዷል፡፡ጤናማ አፈር የሚባለው በቂ የሆነ ውኃ፣ አየርና ረቂቅ ተህዋሲያንን በውስጡ መያዝ ሲችል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ባለመሟላታቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት አሲዳማ እንደሆነ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በዚህ ረገድ የጥናትና ምርምር ሥራ በማከናወን አፈርን ለማከም በሰሜን ሸዋ ዞን ከ81 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ጥቅም ላይ እንደሚውል የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ የመምሪው ምክትል ኀላፊ ሰለሞን ቀለሙ እንደገለጹት በዞኑ 68 በመቶ የሚኾነው መሬት አሲዳማ አፈር ነው፡፡

በዚህም በዞኑ ከ100 ሺ ኩንታል በላይ ምርት በአሲዳማ አፈር ምክንያት በየዓመቱ እንደሚቀንስ ጥናት መደረጉን ነው ኀላፊው የገለጹት፡፡ ችግሩን ሊፈታ የሚችል የተቀናጀ መፍትሔ ለመውሰድም ባለሙያዎችን የማሠልጠን እና ሙያዊ ትኩረት የተሰጠበት ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ምክትል መምሪያ ኀላፊው የተናገሩት፡፡

የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የአፈር ሳይንስ ባለሙያ አሰፋ አዳነ (ዶ.ር) አሲዳማ አፈር ሀገራዊ ችግር ነው ብለዋል። ችግሩን ለመቅረፍ በአፈር ላይ ምርምር ለሚያደረጉ ተቋማት አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላትና ጉዳዩን የትኩረት አጀንዳ ማድረግ እነደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ ደግሞ በአፈር ለምነትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ያደረጉ የጥናት ውጤቶችን በመጠቀም አሲዳማ አፈርን ለማከም ዘመቻ ማድረግ እንደሚገባም ነው ባለሙያው የጠቆሙት፡፡ ከዚህ በፊት አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ሥራ ተከናውኖ የምርታማነት መጠን መጨመር መቻሉም ተገልጾል፡፡

ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አርሶአደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ ሥራን እያከናወኑ ነው” የደሴ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ
Next articleፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ነበረባት የተባላቸው ሄሊኮፕተር ውስጥ ምንም ዓይነት የመትረፍ እድል እንደሌላ ተገለጸ ።