
ደሴ: ግንቦት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ 26 የቀበሌ አሥተዳደሮች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል 8ቱ ከዚህ ቀደም የገጠር ቀበሌ የነበሩ እና ወደ ከተማ አሥተዳደሩ የተካተቱ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ በሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶአደሮች በንቃት እየተሳተፉ እና ውጤት እያስመዘገቡ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
ወጣት አርሶአደር አንዋር ሁሴን እና አርሶአደር አሊ ሙሄ በደሴ ገራዶ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶአደሮቹ ካለፉት ዓመታት በተሻለ መንገድ የባለሙያ ምክር በመቀበል እና በቂ የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ግብአት በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት በበጋ መስኖ ካለሙት ስንዴ ማግኘታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የዋግ በሽታ ፈተና ሆኖባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል። የባለሙያን ምክረ ሀሳብ መሰረት ባደረገ መልኩ እስከ ሦስት ጊዜ ኬሚካል ርጭት በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደተቻለም ጠቁመዋል። ዛሬ ላይ ለመታጨድ የበቃ አዝመራ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በተቃራኒው የኬሚካል ርጭቱን ያልተገበሩ ውስን አርሶአደሮች ምርት አልባ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የደሴ ከተማ አሥተዳደር እንዶድ በር ቀበሌ የመስኖ ልማት ባለሙያ ሰለሞን አሰፋ አርሶአደሮች የባለሙያን ምክረ ሀሳብ የመቀበል ፍላጎት ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን አንስተዋል፡፡ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያን የመጠቀም ልምዱም እንዳደገ ገልጸዋል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ እዩኤል ሙሉዬ 4 መቶ 8 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን አሳውቀዋል። 4 መቶ 50 ኩንታል ምርጥ ዘር እና 1 ሺህ 1 መቶ 26 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶአደሮች እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው ከከተማ ልማት ሥራዎች ጎን ለጎን የግብርና ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ በከተማ እና በገጠር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!