👉የፋሽስቱ ግፍ

43

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ሸዋ በሚገኘው በደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት፣ ካሕናት፣ ዲያቆናት እና የአካባቢው ምዕመናን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈጸሙን የታሪክ መጻሕፍት ያስታውሱናል፡፡ ይሕ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ ፋሽስት ኢጣሊያ የፈጸመው ጭካኔ በዓለም ታሪክ ጥቁር መዝገብ ውስጥ አንዱ ኾኖ ሰፍሯል።

ምንም እንኳን ጣሊያን የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት መንፈስ ለመስበር “በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያንን ማውደም- ይቅደም ” ብለው ቢነሱም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ ቆራጥ አባቶች ደግሞ በአንድ እጃቸው መስቀል በመያዝ እና ሌሎችንም ሀገር ወዳዶች በማስተባበር በፋሽስቱ ላይ:-

“ወግጅልኝ ድጓ ወግጅልኝ ቅኔ፣
ወንዶች ከዋሉበት እውላለኹ እኔ”

እያሉ ሀገራቸውን ከጠላት ለመከላከል በርሃ መውረዳቸው ጣሊያኖችን ረፍት ነሷቸው፡፡ በተለይም ጣሊያኖች የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በግራዚያኒ ላይ በተቃጣው የመግደል ሙከራ ዋነኞቹ ተሳታፊዎች አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉ አስቆጥቷቸው ነበር፡፡ በጣሙን የፋሽስቱ ጦር አርበኛው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ የፍቼ ተወላጅ ናቸውና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸውም ብለው ጠረጠሯቸው፡፡

ታዋቂው አርበኛ ኃይለ ማርያም ማሞ ከገዳሙ መነኮሳት ጋር ይገናኛል መባሉ ደግሞ ጣሊያኖች በደብረ ሊባኖስ ላይ የዘንዶ ዓይናቸውን እንዲጥሉበት አደረጋቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ደብረ ሊባኖስ ገዳም የጣሊያኖች የጥፋት ትኩረት ኾኖ ተፈረጀ፡፡ እናም ለአያሌ ገዳማት መመሥረት ምክንያት የኾነውን የደብረ ሊባኖስን ገዳም ለማጥፋት ሲያጠፉትም ሌላውን ሊያስደነግጥ በሚችል መልኩ በአሰቃቂ ኹኔታ እንዲኾን ወሰኑ፡፡

በዚህም መሠረት ግራዚያኒ ያቀናበረውና ጄኔራል ማለቲ የመራው ጦር ግንቦት 10 ቀን 1929 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወረደ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐጽም የተከናወነበትን በዓል ለማክበር የተሰበሰቡትን ምእመናንና መነኮሳትን መጨፍጨፍም ጀመረ፡፡ ዘ ማሳከር ኦፍ ደብረ ሊባኖስ መጽሐፍ እንዳስነበበው በጫጋል፣ በውሻ ገደል፣ በሥጋ ወደሙ ሸለቆና በደብረ ብርሃን አጠገብ በእንግጫ በተከናወነው ጭፍጨፋ ገና ነፍስ ያላወቁ ሕጻናት የቆሎ ተማሪዎችን ጨምሮ እስከ 2 ሺህ 201 የሚደርሱ ምእመናንና መነኮሳት በግፍ ተረሸኑ፡፡

በዚህም ሳያበቃ በገዳሙ የነበሩ መጻሕፍት፣ የከበሩ ዕቃዎች፣ ነዋያተ ቅድሳት፣ ገንዘብ እና ሌሎች ንብረቶች ተዘረፉ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ጦር በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ ግፍ በትሩን ያሳረፈው በዚህ ሳምንት ግንቦት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ነበር።

👉 የዋርሶ መመስረት

ዋርሶ፤ የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ለፖለቲካ እና ወታደራዊ ኅብረት ሲሉ ግንቦት 6 ቀን 1947 ዓ.ም ያቋቋሙት የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኅብረት ነበር። በሌላ ስሙ የኮሚኒስት ሀገሮች ወታደራዊ ጥምረትም በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ጥምረት በ1949 ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ሌሎች ስምንት የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ስለመሰረቱ ይህን እንዲገዳደር በማሰብ ነው፡፡

በዋርሶ ስምምነት የመጀመሪያዎቹ ፈራሚ ሀገራት ሶቭየት ኅብረት፣ አልባኒያ፣ ፖላንድ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ሃንጋሪ፣ ቡልጋሪያ፣ ሮማኒያ እና የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ናቸው። የዋርሶው ስምምነት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቁት የሶቭየት ወታደሮች በቀጣናው እንዲሰፍሩ ሕጋዊ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በምሥራቅ አውሮፓ መንግሥታት በኩል ነፃ የውጭ ፖሊሲ ላይ ገደቦችን በመደንገግ የሶቭየት ወታደራዊ እና የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራትን የፖለቲካ የበላይነት ለማጠናከር አገልግሏል።

በስምምነታቸው መሠረት ከአባል ሀገራት አንዱ ጥቃት ቢደርስበት እርስ በእርስ ለመከላከል ቃልም የገቡበት ነው፡፡ ይሁንና በአባል ሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ላለመግባትም ተስማምተዋል፡፡ በቡድን ውሳኔ የሚሰጠውም በአብላጫ ድምጽ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረው የዋርሶ ስምምነት የተፈረመው በዚህ ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 1947 ዓ.ም እንደነበር ከኦፊስ ኦፍ ዘ ሂስቶሪያን ዶት ጅኦቪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

👉 የፈንጣጣ ክትባት ሙከራ

ፈንጣጣ ከሰው ወደ ሰው ተላላፊ የኾነ ገዳይ ቫይረስ ነው። በሽታው በዓለም ላይ የበርካታ የሰው ሕይዎትን ቀጥፏል፡፡ ይህን የጥፋት በትሩን በአርምሞ ያጠኑት ዶክተር ኤድዋርድ ጄነር ግንቦት 6 ቀን 1741 ዓ.ም በክትባት የሚሠጥ መድኃኒት ፈበረኩለት፡፡ እኝህ እንግሊዛዊ ሐኪም እና ሳይንቲስት ፈንጣጣን የሚዋጋ መድኃኒት በመሥራታቸውም በምዕራቡ ዓለም ሕዝብ ዘንድ “ጄነር ኢሚውኖሎጂስት ” ተብለው ይጠራሉ፡፡ “በሽታ ተከላካዩ ሳይንቲስት ” ማለት እንደኾነ ይነገራል፡፡

ጄነር ለበሽተኞች የፈንጣጣ ክትባትን ከመስጠታቸው በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው ይሞቱ ነበር፡፡ ክትባቱ መሰጠት በተጀመረ ማግሥት ክትባቱን ከወሰዱ 15 በመቶ ሰዎች ውስጥ 10 በመቶ የሚኾነውን ሕዝብ ከሞት ታድጓል፡፡ በዶክተር ኤድዋርድ ጄነር የተጀመረው ክትባት አድጎ በ1980 ዓ.ም ፈንጣጣ በመላው ዓለም መወገዱን የዓለም ጤና ድርጅት ማስታወቁን ልብ ይሏል፡፡

ናሽናል ኢንስቲትዩትስ ኦፍ ኽልዝ ዶት ጅኦቪ እንዳስነበበው ትኩሳት፣የጡንቻ ሕመም፣ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጀርባ ህመም እና ማስታወክ የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡ ታዲያ ለዚህ ገዳይ በሽታ ፍቱን ክትባት የተፈበረከው ግንቦት 6 ቀን 1741 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሾለ ኢትዮጵያ ተፋቀሩ፣ በአንድነትም ኑሩ”
Next article“አርሶአደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ ሥራን እያከናወኑ ነው” የደሴ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ