
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ብልኾች ትናንትን ይረዳሉ፣ ዛሬን ያሳምራሉ፣ ነገንም ይተነብያሉ። ጥበብ የተቸራቸው በዘመናቸውም፣ ያለዘመናቸውም ስለ ሀገራቸው ያስባሉ፣ ይጠበባሉ፣ ይጨነቃሉ።
ልጆቻቸው፣ ወዳጆቻቸው በፍቅር የሚኖሩበትን፣ በአንድነት የሚጸኑበትን፣ የሚከባበሩበትን፣ ኮርተው ሀገር የሚያኮሩበትን፣ ጠላቶቻቸውን ድል የሚመቱበትን፣ ሉዓላዊነታቸውን የሚያስከብሩበትን፣ ነጻነታቸውን የሚያጸኑበትን፣ ሠንደቅ ዓላማቸውን በኩራት የሚያውለበልቡበትን ብልሃት ያስተምራሉ፣ ጥበባቸውን ይነግራሉ፣ ቃል ኪዳናቸውንም ይሠጣሉ፣ አደራቸውንም ያስቀምጣሉ።
በዘመናቸው ኃያል ታሪክ ይሠራሉ፣ ያለመታከት ስለ ሀገር ይፋጠናሉ፣ በዘመናቸውም ያለ ዘመናቸውም ስለ ሀገራቸው ክብር አብዝተው ያስባሉ። እነርሱ እኔ ካለፍኩ ተተኪ ይጨነቅበት፣ ልጅ የልጅ ያስብበት፣ እኔ ሮጫዬን ጨርሻለሁ፣ በዘመኔም መልካሙን ነገር አድርጌያለሁ ብለው ዝም አይሉም። ይልቅስ አንድነት እንዳይፈርስ፣ ፍቅር እንዳይረክስ፣ ነፃነት እንዳይጣስ፣ ሉዓላዊነት እንዳይገረሰስ ለልጆቻቸው መልካሙን ምክር ይመክራሉ፣ የአደራ ቃላቸውንም ያስቀምጣሉ እንጂ።
ከአንድነት የምታጎድለውን፣ ከሀገር ፍቅር የምታሳንሰውን፣ ወንድምን በወንድሙ ላይ የምታስነሳውን፣ ደም የምታፋስሰውን፣ አጥንት የምታከሳክሰውን ጥልና ጥላቻን ጣሏት።
የማትታበየውን፣ ጥላቻ የማታውቀውን፣ ከራስ በላይ የምታሳስበውን፣ ለሌሎች መስዋዕት ለመኾን የምትፈቅደውን፣ ወንድም ከወንድሙ ጋር በደስታ የምታኖረውን፣ አንድነትን እንደ ዓለት የምታጠጥረውን፣ ሰላም እና ደስታ የምትሰጠውን ፍቅርን ገንዘባችሁ አድርጓት።
ስለ ኢትዮጵያ ብላችሁ ተፋቀሩ፣ ስለ ተወደደችው ምድር ብላችሁ አንድነታችሁን አጠንክሩ፣ የተስፋ ምልክት ስለኾነችው ሠንደቅ ብላችሁ በፍቅር ኑሩ። እርሷ መስዋዕትነት የተከፈለባት፣ የአበው እና እመው ደምና አጥንት ያጸናት፣ የጀግኖች ክንድ የከለላት፣ ስለ ነፃነቷ፣ ስለ ታሪኳ እልፍ አዕላፍ መስዋዕት የተከፈለባት ሀገር ናትና።
እኒያ አባት ኾነው ሳለ በእናት ስም የሚጠሩት፣ አባዬ መባል ሲገባቸው እምዬ የሚባሉት፣ እንደ እናት የሚወደዱት፣ እንደ አባት የሚከበሩት፣ መጠጊያ ጋሻ፣ መኩሪያ መከታ የሚኾኑት፣ በዘመናቸው አያሌ ታሪክን የጻፉት፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የታሪክ ውርስ እና ቅርስ ያስቀመጡት፣ ነፃነትን በደም ማሕተም አትመው፣ መሠረቱን አለት ላይ አጽንተው የሰጡት፣ የከበረች ሀገርን፣ የታፈረች ሠንደቅን ያወረሱት ግርማዊ ዳግማዊ ምኒልክ ከእርሳቸው በኋላ ለሚነሱት ነገሥታት፣ ከእርሳቸው በኋላ ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን የአደራ ቃል አስቀምጠው ነበር፡፡
ተክለጻድቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ሲጽፉ “ንጉሠ ነገሥቱ ሕመም እንደጸናባቸው እና እርጅና እንደተጫናቸው በተረዱት ጊዜ ሃሳባቸው እና ስጋታቸው ያስተካከልሁት የኢትዮጵያ አንድነት ይፈርስ ይኾን? በዙሪያዬ በኔ ሰበብ በንጉሠ ነገሥትነቴም ምክንያት ባንድ ሥልጣን የተሳሰሩት መሳፍንት እና መኳንንት እኔ ስሞት ተከፋፍለው በመዋጋት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አደጋ ይመጣ ይኾን? የሚል ነበር፡፡ ይህን ስጋት የጣለባቸው ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ሳይቋረጥ እስከ ዘመናቸው የደረሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው” ብለዋል፡፡
ምኒልክ ለዚህ ሁሉ ስጋታቸው መፍትሔ ብለው ያመኑበት ለመኳንንቱ እና ለመሳፍንቱ ምክር መምከር፣ አደራ መስጠት፤ ከዚያም ከእርሳቸው ቀጥሎ ያለውን ዙፋናቸውን የሚረከብ ወራሻቸውን ማስታወቅ ነበር፡፡
ምኒልክ መኳንንቱን እና መሳፍንቱን በቤተ መንግሥት ግቢ ሰብሰበው እንዲህ አሏቸው፡፡ “እኔ ዳግማዊ ምኒልክ በሸዋ 24 ዘመን ነገሥሁ፣ ከነገሥሁ እስካሁን አንድ ቀን አላረፍሁም፡፡ ለሕዝቡ እና ለመንግሥቴ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማግኘት ወሰኔም የሕንድ ውቅያኖስ ኾነ፡፡… አሁንም ይኸውና በእግዚአብሔር ኃይል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ተኾንሁ 17 ዘመኔ ኾነ፡፡ ድምሩ 41 ነው፡፡ ይህ ሁሉ መኾኑ ኢትዮጵያ በአንድ ፈቃድ ብታድር እና በአንድ ትዕዛዝ (ስልጣን) ብትኾን ነው፡፡ አንድነት ከብረት ይጠናልና ተረቱም “ከአንድ ብርቱ ሁለት ሰነፍ ይሻላል” ነው የሚል፡፡ አያቶቻችን አንድነት ቢኾኖ ባሕርን ተሻግረው ገዙ፡፡ ኢትዮጵያ አንድነት ኾና ከቶ ለጠላት ተሸንፋ አታውቅም፡፡ በታሪክም የለ፡፡
ስለዚህ ምክር ነው የሰበሰብኋችሁ፡፡ አንድነት እንዲጠና ብዬ፡፡ ምን አልባት ያ መለያየት ከእኔ በኋላ ይመጣና ሀገር እንዳይጠፋ ጠላት ደስ እንዳይለው፤ ሀገራችን እንዳይሄድ ሕዝባችን ወደ ግዞት እንዳይገባ፣ የሠራሁት እንዳይፈርስ ያቀናሁት መልሶ እንዳይጠፋ ብዬ ብፈራ ነው፡፡
ስለዚህ በኋላ ወራሼን ላሳውቃችሁ ከልጄ ከወይዘሮ ሸዋረጋና ከራስ ሚካኤል የተወለደው ኢያሱ ነው የአልጋዬ ወራሽ፡፡ እርሱን እወቁ እርሱን ተከተሉ አሉ፡፡ ግርማዊ ዳግማዊ ምኒልክ ለመሳፍንቱ እና ለመኳንቱ ብቻ ምክር ሰጥተው ዝም አላሉም፡፡ ይልቅስ ሕዝብም ምክራቸውን እና የአደራ ቃላቸውን ይስማ ዘንድ ወደዱ የወደዱትንም አደረጉ፡፡
ተክለጻድቅ መኩሩያ በታሪክ መጻሕፋቸው ጠቅላላው ሕዝብ ይህንኑ እንዲሰማ ስላስፈለገ በግንቦት 10 ቀን 1901ዓ.ም በጃንሆይ ሜዳ ታላቅ ስብሰባ ተደርጎ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እና እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ራሶች፣ ደጅአዝማቾች፣ ሚኒስትሮች እና የውጭ ሀገር መልእክተኞች ባሉበት በይፋ ተነገረ ብለዋል ጽፈዋል፡፡ ጰውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ግንቦት 10 ቀን 1901ዓ.ም ለሕዝቡ የተነገረውን የምኒልክ አደራ የምኒልክ የመጀመሪያው የኑዛዜ ቃል ነው ብለው ጽፈዋል፡፡
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው በ1901 ዓ.ም ግንቦት 10 ቀን አዲስ አበባ ጃን ሜዳ በሚባል ስፍራ ጉባኤ ተደርጎ ዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ያዘዙት ቃል ይህ ነው በማለት ቃላቸውን አስፍረዋል፡፡
“የሀገሬ የኢትዮጵያ ሰዎች ልጆቸ ወዳጆቼ ምክር ልምከራችሁ፤ አፄ ቴዎድሮስ የሞቱ ጊዜ ከእሳቸው ጋር የነበረው ሰው ሁሉ የአንዱን ሀገር አንዱ እደርባለሁ፣ አንዱን ገድዬ እኔ ጌታ እኾናለሁ እያለ ሁሉም ላይረባ ተላልቆ ቀረ፡፡ ከዚያም በኋላ የአጼ ዮሐንስ ሰው የኾነውን የምታውቁት ነው፡፡ ባገር በሽታ ሳይገባበት ሌላ የባዕድ ጦር ሳይነሳበት በምቀኝነት እርስ በእርሱ እንደተላለቀ አይታችሁታል፡፡
አሁንም ልጆቼ ወዳጆቼ፣ አንዱ በአንዱ ምቅኝነት ይቅር፡፡ ያንዱን ሀገር አንዱ እኔ እደርበዋለሁ እንዳትባባሉ፤ እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኋችሁ እናንተም ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ፡፡ እናንተ አንድ ልብ ከኾናችሁ በምቀኝነት እርስ በእርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ሀገራችንን ኢትዮጵያን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም፡፡ ክፉ ነገር ሀገራችንን አያገኛትም፡፡ ነፋስ እንዳይገባባችሁ ሀገራችሁን በየአላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋጋፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተደንበር መልሡ፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት በአንድ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድ እና ደምበር ቢጋፋ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፡፡ ያ ጠላት በመጠባት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ፡፡ እስከየቤታችሁ እስቲመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ፡፡
ይህንን ምክር ለእናንተ መስጠቴ እኔማ ይህንን ያህል ዘመን ገዝቼ የለምን፡፡ ነገር ግን ሰው ነኝና እንግዲህ እስከ ስንት ያህል ዘመን እቆያለሁ ስል ነው፡፡ አሁንም እኔ እንደተመኘሁት የእግዚአብሔር ፈቃዱ ኾኖ ልጄን ቢያቆምላችሁ ከልጄ ጋር ሆናችሁ ሀገራችሁን ጠብቁ አደራ ብያችኋለሁ፡፡ አደራ የሚያኖሩበት ሰው የታመነ ስለኾነ ነው፡፡ አሁንም እኔ እናንተን አምኘ ልጄን አደራ ብዬ እሰጣችኋለሁ፡፡ አሳድጉት፣ በብልሐት ምከሩት፣ በጉልበት አግዙት በምክር ደገፉት፡፡ ልጄን አደራ መስጠቴ ከልጄ ጋር ኢትዮጵያን አደራ ጠብቁ ማለቴ ነው፡፡
ተስማምታችሁ የኢትዮጵያ ደምበር እንዲሰፋ እንጂ አንድም ጋት መሬት እንዳይጠብ አድርጉ፡፡ ጠብቁ፤ አልሙ፡፡ የደጊቱ ሀገራችን የኢትዮጵያ አምላክ ይግዛችሁ ይጠብቃችሁ፡፡
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ የንጉሡን አደራ በተመለከተ ሲጽፉ “እንዲህ ያለው ቃል ልብ ላለው ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያን የወደደ፤ የኢትዮጵያን መልማት፣ የኢትዮጵያን ደስታ፣ የኢትዮጵያን ትልቅነት የወደደ ሰው ይህንን የጃንሆይን ቃል አዝኖ ተክዞ መቀበል ይገባዋል፡፡ አዝኖ ተክዞ ማለቴ እንዲህ ያለ እናት ንጉሥ የሞቱን ነገር አስቦ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን አውቆ እንዲህ ያለ የተገባ፣ የጣፈጠ፣ ከልብ ጠልቆ የሚገባ፣ ምክር ለሕዝቡ መስጠቱ ተሞቱም በኋላ ለኢትዮጵያ የሚኾነውን፣ ለሀገር የሚጠቅመውን፣ ለሕዝቡ የሚያከብረውን ነገር ማሰቡና መምከሩ እጅግ ያሳዝናል ማለቴ ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ኾይ አንድነትን ጠብቋት፣ ፍቅርን አታርክሷት፣ ለሀገራችሁ ሰላምን ስጧት፡፡ ተድላና ደስታንም አብዙላት፡፡ የታመነ ሰው አደራ እንደሚሰጠው ሁሉ የአንድነትን አደራ ጠብቁ፤ በአደራ ቃልም ተጠበቁ፡፡ የኢትዮጵያ አደራ በእናንተ ዘመን ላይ ወድቋል፡፡ አደራው ሲጠበቅ፣ አንድነት ሲጠብቅ ሀገር ሰላም ትኾናለች፣ በጠላቶቿ ትፈራለች፡፡ በግርማዋ ታስፈራለች፡፡ በክንዷ ትቀጣለች፡፡ በወዳጆቿም አብዝታ ትወዳዳለች፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!